
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ሰላምን ዘላቂ ከማድረግ ጎን ለጎን የልማት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር እና የምስራቅ አማራ ኮማንድፖስት ምክትል ሰብሳቢ አብዱ ሁሴን ገልጸዋል። የምሥራቅ አማራ ኮማንድፖስት የሰላም እና የፀጥታ ሥራዎችን በኮምቦልቻ ከተማ ገምግሟል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር እና የምሥራቅ አማራ ኮማንድፖስት ምክትል ሰብሳቢ አብዱ ሁሴን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በክልሉ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ክልሉን ካጋጠመው ችግር ታድጓል ብለዋል፡፡ የፀጥታ መዋቅሩ በቅንጅት ባካሄደው ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴ በክልሉ ሰላም ማስፈን መቻሉን ተናግረዋል።
በዚህም የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል ነው ያሉት። በክልሉ የተገኘውን ሰላም ከኅብረተሰቡ ጋር በመተባበር ዘላቂ ከማድረግ ባሻገር የልማት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውንም አቶ አብዱ ሁሴን ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡም የጽንፈኞችን ሀገር የማፍረስ ሴራ በመረዳት ከመንግሥት ጎን ተሰልፎ ሰላሙን በማስከበር እና በሌሎችም ዘርፎች እያደረገ ያለውን ንቁ ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!