ናሚቢያ ኤች.አይ.ቪ እና የጉበት ቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ለማድረግ እየሠራች ያለችው ሥራ ከአፍሪካ ቀዳሚ እንዳደረጋት የዓለም ጤና ድርጅት ገለጸ።

13

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በዓለም ካለው የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ስርጭት ከግማሽ በላይ የሚኾነውን የሚሸፍኑት የአፍሪካ ምሥራቃዊ እና ደቡባዊ አካባቢዎች መኾናቸውን የአፍሪካ ኒውስ ዘገባ ያመለክታል። በተጨማሪም ሁለት ሦስተኛ የሚኾነው የዓለማችን የጉበት ቫይረስ ሥርጭት በአፍሪካ የሚገኝ መኾኑ ተዘግቧል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተራድኦ ተቋም (ዩኤንኤአይዲኤስ) የምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር አን ጊቱኩ ሾንግዌ በናሚቢያ የተሠራው ስኬታማ ሥራ በሌሎች አካባቢዎች ባለመሠራቱ ለበርካታ ሕጻናት መድረስ አለመቻሉን ተናግረዋል። ይህን ችግር በመቅረፍ ረገድ ናሚቢያ ፍትሐዊ በኾነ መንገድ የሠራችው ሥራ ሁሉንም ሕጻናት ያለ ልዩነት ተጠቃሚ እያደረገ የሚገኝ በመኾኑ ስኬታቸው አኩሪ መኾኑን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል። ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትንም የሚያነቃቃ መኾኑን ገልጸዋል።

በሀገሪቱ ለነፍሰ ጡር እናቶች የኤች አይ ቪ ምርመራ ማድረግ የተለመደ ነው። በመኾኑም በምርመራ በሚረጋገጥ ውጤት መሠረት በሚደረግ የሕክምና ድጋፍ ባለፉት 20 ዓመታት 70 በመቶ የሚኾነውን የቫይረሱን ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ እድል መቀነስ መቻሉም ተነግሯል። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2022 አራት በመቶ የሚኾኑት ሕጻናት ብቻ ከቫይረሱ ጋር ከሚኖሩ እናቶቻቸው ቫይረሱ እንደተላለፈባቸው እና 80 በመቶ የሚኾኑት ሕጻናት በጊዜው የጉበት ባይረስ ክትባት በሰዓቱ ማግኘት መቻላቸው የተገለጸ ሲኾን ችግሩን ለማስወገድ ሀገሪቱ ጥሩ የስኬት መንገድ ላይ እንደምትገኝ ተገልጿል።

ናሚቢያ መሠረታዊ የጤና ጥበቃ አገልግሎትን ከቅድመ ወሊድ፣ ከልጆች ጤና አጠባበቅ እና ከሥርዓተ ፆታ ጋር አስተሳሥራ የምትሠራ አፍሪካዊት ሀገር ስትኾን ነጻ የጤና ጥበቃ አገልግሎት እና ድጋፍም ታቀርባለች። የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው መሥፈርት መሠረት የጉበት ቫይረስን በመከላከል ረገድ የብር ማዕረግ ደረጃ እና የኤች. አይ . ቪ ቫይረስ ሥርጭትን በመቀነስ ደግሞ የነሃስ ማዕረግ ደረጃን ተቀዳጅታለች።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል ”በኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ የ312 ባለሀብት ኢንዱስትሪዎችን ችግር በመፍታት ወደ ማምረት ተግባር ማሸጋገር መቻሉን ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
Next articleየፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄን በመቀላቀል የ5 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ።