
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ”በኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ የ312 የባለሀብት ኢንዱስትሪዎችን ችግር በተቀናጀ መንገድ ለይቶ በመፍታት ወደ ማምረት ተግባር እንዲሸጋገሩ ማድረግ መቻሉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገልጸዋል። ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እንደገለጹት ”የኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በአልሚ ባለሃብቶችና በመንግሥት ተቋማት መካከል ያለውን ቅንጅታዊ አሠራር በማጠናከር ውጤት እንዲመዘገብ እያስቻለ ነው።
በዚህም ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በተከናወነ ቅንጅታዊ አሠራር የ312 ባለሀብት ኢንዱስትሪዎች በሥራ ሂደት አጋጥሟቸው የነበሩ ችግሮችን መፍታት መቻሉን ተናግረዋል። የኢንዱስትሪዎቹን ችግር በመፍታትም ወደ ማምረት ማሸጋገር የተቻለ ሲሆን፤ በዚህም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካትና የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ገልፀዋል።
ኢንዱስትሪዎቹ ወደ ማምረት የተሸጋገሩት ከመሬት፣ ከብድርና ከመሰረተ ልማት ጋር የተያያዙ መሰረታዊ ጥያቄዎች ”በኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በተወሰደው ቆራጥ እርምጃ መፍታት በመቻሉ መሆኑንም አስታውቀዋል። ወደ ማምረት የተሸጋገሩት ኢንዱስትሪዎችም ከ82 ሺህ 300 በላይ ለሚሆኑ ሥራ እጥ ወገኖች ቋሚ የሥራ እድል መፍጠር ያስቻሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
”የኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ክልሉ ካጋጠመው የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግር ከፈጠረው ጉዳት ፈጥኖ በማገገም የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያገዘ ውጤት እንዲመዘገብ እንዳስቻለም ርእሰ መሥተዳድሩ አረጋግጠዋል። በክልሉ እየተገኘ ያለውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠልም ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት የሚተገበር የመካከለኛ ጊዜ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን አስታወቀዋል።
በተጨማሪም የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመለየትና በመፍታት ከሌላው የመደበኛ ሥራ በተለየ መልኩ ለመምራት አደረጃጀት በመፍጠርና የሰው ኀይል በመመደብ እየተሠራ እንደሚገኝም አብራርተዋል። አጠቃላይ ክልሉ በግብርና፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች እምቅ ፀጋ አለው ያሉት አቶ አረጋ፤ ፀጋዎችን በማልማት ኢኮኖሚያዊ እድገትን ማፋጠንና የሕዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
እንደ ርእሰ መሥተዳድሩ ማብራሪያ ፀጋዎችን በመለየት፣ የምርት አይነቶችን በመወሰንና አምራች ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ በማስገባት በክልሉ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ ተቀርጾ እየተተገበረ እንደሚገኝም ገልጸዋል። ኢዜአ እንደዘገበው በዚህ ዓመት በ28 የኢንዱስትሪ መንደሮች ከ3ሺህ 200 ሄክታር በላይ መሬት በመለየትና መሰረተ ልማት በማሟላት የ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄን ማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥት በኢንዱስትሪ መንደሮች መሰረተ ልማት እያሟላ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ባለሃብቶች ሼድ በመገንባትና ማሽን ተክለው ፈጥነው ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!