ለሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዕጩ ምክትል ዋና ዕንባ ጠባቂ እና ዕንባ ጠባቂዎች ምዝገባ 480 ተጠቋሚዎች መመዝገባቸው ተገለጸ፡፡

12

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴው ባካሄደው 2ኛ መደበኛ ሥብሠባ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዕጩ ምክትል ዋና ዕንባ ጠባቂ እና ዕንባ ጠባቂዎች ምዝገባ አፈፃፀም ሪፖርት እና ዝርዝር የምልመላ መስፈርቶች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
በሂደቱም ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ መመዝገቡን የገለጸው ኮሚቴው በሪፖርቱም ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴው 480 ተጠቋሚ ዕጩዎችን መመዝገቡንም ነው የገለጸው፡፡

የዕጩ አቅራቢ ኮሚቴው ሂደቱ የደረሰበትን ደረጃ የአፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦለት ተወያይቷል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሠ ጫፎ በምዝገባ ሂደቱ በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ሕዝቡ ያደረገውን ተሳትፎ እና ባለሙያዎቹ በእረፍት ቀናት ሳይቀር ለመመዝገብ ያደረጉትን ጥረት አድንቀዋል፡፡
ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴው በሚያስቀምጠው አቅጣጫ እና በምልመላ መሥፈርቱ መሠረት በፍጥነት እንዲከናወንም አሳስበዋል፡፡

በሪፖርቱ እንደተመላከተው ለምክትል ዋና ዕንባ ጠባቂ 200፣ ለዘርፍ ዕንባ ጠባቂ 85 እና ለሴቶች፣ ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞች እንዲሁም አረጋውያን ዕንባ ጠባቂ 195 በድምሩ 480 ተጠቋሚዎች መቅረባቸውን የኮሚቴው ጸሐፊ ዕውነቱ አለነ ገልጸዋል። የምዝገባ ሂደቱ ተጠቋሚ እጩዎችን ለመቀበል በስልክ፣ በኦን ላይን እንዲሁም በጥቆማ ለሚያቀርቡ ጠቋሚዎች የመጠቆሚያ ሳጥኖች በማዘጋጀት እና በሚዲያ ሽፋን መሠጠቱን አቶ ዕውነቱ ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት አብራርተዋል።

ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴው በጥልቀት ተወያይቶ ውድድሩን በውጤታማነት ለማጠቃለል የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ማሳለፉንም ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ኢዜአ እንደዘገበው ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴው ተጠቋሚዎችን በመለየት እና በጥንቃቄ በማወዳደር የተሻለ ውጤት ያመጡትን ዕጩዎች ለሕዝብ በይፋ እንደሚገልጽም ተመላክቷል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በተሠራው ቅንጅታዊ ሕግ የማስከበር ሥራ በዞኑ አንጻራዊ ሰላም እየታየ ነው” የምሥራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ዋለ አባተ
Next articleበአማራ ክልል ”በኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ የ312 ባለሀብት ኢንዱስትሪዎችን ችግር በመፍታት ወደ ማምረት ተግባር ማሸጋገር መቻሉን ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።