“ከኢትዮጵያ ለዓለም የሥራ ገበያ የሚቀርበው የሰው ኀይል ሥልጠና የመዳረሻ ሀገራትን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ሊኾን ይገባል” የዓለም ባንክ

12

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ለወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል። የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ከዓለም ባንክ የምሥራቅ አፍሪካ የማኅበራዊ ጥበቃና ሥራ አተገባበር ሥራ አስኪያጅ ሮበርት ቼዝ(ዶ.ር) ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ እንደገለጹት፤ መንግሥት ለወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ በዚህም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ለማላቅ ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ የማዘመን ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በዓለም ባንክ ድጋፍ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም በመጀመሪያ ዙር የሥራ ላይ ልምምድ ካደረጉ ወጣቶች መካከል 93 በመቶ ከሥራ ጋር ማስተሳሰር መቻሉንም አመልክተዋል፡፡ 18 የሚሆኑ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችን በደረጃ በማሻሻል በከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ውጤታማ ሥራዎች እንደተከናወኑ ገልጸው ባንኩ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፉ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

የዓለም ባንክ የምሥራቅ አፍሪካ የማኅበራዊ ጥበቃና ሥራ አተገባበር ሥራ አስኪያጅ ሮበርት ቼዝ (ዶ.ር) በበኩላቸው፤ በመጀመሪያው ዙር በወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ የተገኘው ውጤት የሚያበረታታ ነው ብለዋል፡፡ ድጋፍ የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ የሚኾን እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በጨረታ ሂደት የሚስተዋሉ መዘግየቶችን በመቅረፍ ባንኩ ለወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል፡፡ ከውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አኳያ የሠለጠነ የሰው ኀይል ለማሰማራት የተጀመሩ ሥራዎችን አድንቀው ለዓለም የሥራ ገበያ የሚቀርበው የሰው ኀይል ሥልጠና የመዳረሻ ሀገራትን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ኾኖ መጠናከር እንዳለበት መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኦማን ማቆያ ጣቢያዎች ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን መካከል 230 ያህሉ ዛሬ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ነቀምቴ ከተማ ገቡ።