
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 25ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) ለምክር ቤቱ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በኢኖቬሽን፣ በቴክኖሎጂ፣ በምርምር እና በዲጂታል ኢኮኖሚ፣ በአቅም ግንባታ እና፣ መሰረተ ልማት ግንባታ በርካታ ሥራዎችን ማከናወን መቻሉን አንስተዋል፡፡ ሚኒስትሩ የኢኖቬሽን፣ የምርምር እና ሥነ ምህዳር ተጠቃሚነትን በማሳደግ የዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የአሠራር ሂደቶችን በመዘርጋት ውጤታማ ሥራዎችን መሥራታቸውን ገልጸዋል።
ሀገራዊ የኢኖቬሽን፣ የቴክኖሎጂ እና የምርምር አቅሞችን ከማጎልበት አኳያ ሰፊ ሥራዎችን መሥራታቸውን ጨምሮ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ እና የኢኖቬሽን መሠረተ ልማት አቅሞችን መለየት እና መረጃዎችን የማደራጀት ሥራዎችን በመሥራት በዘርፉ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ተያይዞም የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝ ልማት ሥነ ምህዳርን በማጎልበት እና በማስፋት ረገድ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ስታርትአኘ ሃሳቦችን በማወዳደር እና ድጋፍ በማድረግ ከዘርፉ የሚገኙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችን እና የሥራ ዕድልን የማሳደግ ሥራዎችን እየሠራን ቢኾንም ግን እንደ ሀገር የጎለበተ የስታርት አፕ ሥነ ምህዳር የሌለ መኾኑን እንደ ችግር ገልጸዋል፡፡ የፖሊሲ ማዕቀፍ፣ የፋይናንስ ድጋፍ ማዕቀፍ እና የሕግ ማዕቀፍ የሚያስፈልገን በመኾኑ እዚህ ላይ ልንሠራ ይገባል ነው ያሉት።
ሀገራዊ የዲጅታል ኢኮኖሚ ልማትን በማሳደግም ኾነ ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶችን ወደ ሥራ በማስገባት ዜጎች ተጠቃሚ እንዲኾኑ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ወሳኝ የኾኑ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በማስፋት እና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በማልማት ወደ ማኅበረሰቡ እንዲደረሱ ሥራዎችን እየሠራን ነው ሲሉም ጠቁመዋል።
በምክር ቤቱ የሰው ሃብት ልማት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ.ር) ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ እና ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን መሥራቱን ጨምሮ የስፔስ እና ስፔሻል መረጃዎችን ለሀገር ልማት እንዲውሉ ብሎም የኢንፎርሜሽን እና ቴክኖሎጂ የአሠራር ሥርዓትን በመዘርጋት ካነሷቸው ውስጥ ናቸው።
ይህ ዘርፍ ትልቅ አቅም ያለው በመኾኑ የመንግሥትን የንግድ ሥራ በቴክኖሎጂ ከመደገፍም ባሻገር የዲጂታል ኢኮኖሚ መሠረተ ልማት ከመገንባት ረገድ እጥረቶች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡በሌላ በኩል የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ቴክኖሎጂ መር ፈጣን ዕድገት የማስመዝገብ ስትራቴጂን በተሻለ ውጤታማ ለማድረግ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
ስታርት አፖችን ከማልማት፣ ከመደገፍ እና በክልሎች ማዕከላትን በመክፈት ሥራ ፈላጊ ወጣቶች አስፈላጊውን አገልግሎት በማግኘት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ያሏቸውን ሃሳቦች መጠቆማቸውን ከኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!