በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ መጣሉን ተከትሎ ከ150 ሺህ በላይ ዜጎች በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙ ተገለጸ።

19

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኬንያ እየዘነበ ያለው ከባድ ዝናብ ያደረሰውን ቀውስ ተከትሎ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በአደጋው ለተጎዱ እና ለተፈናቀሉ ቤተሰቦች የሚውል የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል ገቡ። በሀገሪቱ መዲና ናይሮቢ ከመደበኛው እና ከሚጠበቀው በላይ በኾነ መንገድ ጥቅጥቅ ብለው በተሠሩት እና የጎርፍ አደጋው ሰለባ በኾኑት መንደሮች ተዘዋውረው የተመለከቱት የሀገሪቷ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የ10 ሺህ ሽልንግ ወይም 75 የአሜሪካን ዶላር ለመስጠት እና የፈረሱ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት ቃል ገብተዋል።

የኬንያ መንግሥትም በአደጋው ምክንያት ተዘግተው የነበሩ ትምህርት ቤቶች ከመከፈታቸው በፊት ሁሉንም በአደጋው የተጎዱ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መመደቡን በጉግኝታቸው ወቅት ተናግረዋል። ከ200 በላይ ዜጎችን ለሕልፈት የዳረገው ጎርፍ ያስከተለው ከባድ ዝናብ ባለማቆሙ ምክንያት ትምህርት ቤቶች ይከፈቱበታል ተበሎ የተቀመጠው ጊዜ በማስታወቂያ እስኪነገር ድረስ ለሌላ ጊዜ መተላለፉን ፕሬዚዳንት ሩቶ ገልጸዋል።

የፕሬዚዳንቱ አዋጭ ብሔራዊ የቤት ልማት ፕሮጀክት ለወደፊት በምን ዓይነት መንገድ ከጎርፍ ጋር በተያያዘ ከሚደርስ መፈናቀል እና አደጋ እንደሚከላከል አክለውም አብራርተዋል። በናይሮቢ የአደጋው ሰለባ የኾኑ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደረግ 20 ሺህ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ፕሮጀክትን በቅርቡ እንደሚያበስሩም ፕሬዚዳንት ሩቶ ተናግረዋል።

እንዲህ ዓይነቱ ፕሮጀክት ለዜጎች የመኖሪያ ቤቶችን ማቅረቡ ብቻ ሳይኾን ለወደፊት ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎችን ጭምር ለመከላከል ያግዛል ሲሉ የቤት ልማት ዕቅዳቸውን አሞካሽተውታል። ፕሬዚዳንቱ ለሀገሪቷ ዜጎች ባስተላለፉበት መልእክት ዝናቡ እና የጎርፍ አደጋው መቼ እንደሚያቆም የሚጠቁም እርግጠኛ የአየር ንብረት መረጃ አለመኖሩን አስረድተዋል።

ኬንያ እና ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በጎርፍ እየተመቱ ሲኾን ከ150 ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለው በካምፓ ውስጥ እንዲጠለሉ አስገድዷል። የኬንያ መንግሥት ከዝናቡ አለማቋረጥ ጋር ተያይዞ በግድቦች እና የውኃ ማማዎች አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ አሳስቧል። ይኽን ተከትሎ አብዛኞቹ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ አካባቢውን ለቀው መሄዳቸው ተነግሯል።

በሃገሪቱ ያሉ ሁለት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ መሙላታቸውም ተነግሯል። በምስራቅ አፍሪካ እየጣለ ባለው ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ምክንያት ሌሎች ሀገራትም እየተፈተኑ ይገኛሉ። በታንዛኒያ የተከሰተው ጎርፍ 155 ሰዎችን ለህልፈት የዳረገ ሲኾን በቡሩንዲ፣ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያም ጉዳት እየደረሰ ነው ሲል አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ እንደሚገኝ ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
Next articleየዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የአሠራር ሂደቶችን በመዘርጋት ውጤታማ ሥራዎችን መሥራቱን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡