
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በ2016/17 ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከ19 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ተገዝቶ ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሚኾነው ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ እንደሚገኝ ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ግብርናውን ለማዘመን በተሠራው ሥራ ከ15 ሺህ በላይ ትራክተሮች በግብርና ሥራ ላይ መሳተፋቸውም ተገልጿል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አሥፈፃሚ ከበደ ላቀው እንደገለጹት በ2016/17 የምርት ዘመን አገልግሎት ላይ እንዲውል ከተገዛው 19 ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 25 በመቶ የሚሆነው ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የዋለ ነው ብለዋል። 20 በመቶ የሚኾነው ለበልግ እንደሚውልና 55 በመቶ የሚኾነው ደግሞ ለመኸር ምርት የሚውል ይኾናል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በ2015/16 የምርት ዘመን የተከሰተው የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ችግር በ2016/17 እንዳይከሰት የግዥ ሥርዓቱን የማሻሻል፤ አስቀድሞ የመግዛት፣ ስርጭቱን የመከታተልና የመቆጣጠር ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። ይህ በመደረጉ በቂ የኾነ የአፈር ማዳበሪያ እንዲቀርብ ማስቻሉንም ገልጸዋል፡፡
በዘንድሮው ዓመት ቀደም ብሎ የአፈር ማዳበሪያው እንዲገዛ መደረጉ ጊዜና ጉልበትን ከመቆጠቡ ባለፈ አርሶ አደሮ ተረጋግተው ግብዓቱን በሚፈልጉት ሰዓት በቀላሉ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ስርጭቱ ላይ ሕገ ወጥ አሠራሮች እንዳይኖሩም የሚከታተልና የሚቆጣጠር ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ የሀገሪቱን የግብርና ዘርፍ በማዘመን ምርትና ምታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ ባለው ሥራ የግብርና ሜካናይዜሽንና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም ሥራ እየተከናወነ እንደሆነም አቶ ከበደ አብራርተዋል። በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፤ በበልግና በመኸር እርሻ ላይ ከ15 ሺህ በላይ ትራክተሮች ጥቅም ላይ ውለዋል፤ ለቀጣይ የመኸር እርሻ ቁጥራቸውን በማሳደግ ጥቅም ላይ የማዋል ሥራ እየተከናወነ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የግብርና መካናይዜሽን መሳያዎችን ማለትም ትራክተሮች፤ ኮምባይነሮችና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ከቀረጥ ነፃ በሆነ መንገድ በማኅበራትና በአርሶ አደሮች እንዲገቡ እየተደረገ ነው ያሉት ሥራ አሥፈጻሚው ይህ አሠራርም ቁጥራቸውን እያሳደገው ነው ብለዋል፡፡ ኢፕድ እንደዘገበው ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የግብዓት አቅርቦትን የማሳደግና በወቅቱ የማሰራጨት ሥራ በትኩረት እየተሠራበት ይገኛል ሲሉም አመላክተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!