
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የ2016 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ከሰኔ 14 እስከ 21/2016 ዓ.ም እንደሚሰጥ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ፈተናውን 250 ሺህ ለሚደርሱ ተማሪዎች ለመስጠት ዝግጅት መደረጉም ተገልጿል፡፡ በሚኒስቴሩ የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ሥራ አስፈጻሚ ኤባ ሚጀና (ዶ.ር) እንደገለጹት የዩኒቨርሲ መውጫ ፈተና ተማሪዎች ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ሲወጡ ሊኖራቸው የሚገባውን እውቀት፣ ክህሎት እና አመለካከት ለመለካት የሚሰጥ ነው፡፡
የሚወጡ ጥያቄዎችም የየትምህርት ክፍሎች ምሩቃን እንዲኖራቸው የሚጠበቀውን እውቀት፣ ክህሎት እና አመለካከት መሰረት አድርገው የሚዘጋጁ ናቸው፡፡ሚኒስቴሩ ፈተናውን ለመስጠት አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን ጠቅሰው፤ ፈተናው ተዘጋጅቶ እንዲገመገም ተደርጓል ብለዋል፡፡ ዶክተር ኤባ እንደገለጹት ተፈታኝ ተማሪዎችን መረጃም በመሠብሠብ ላይ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ከዚህ በፊት በኤክስኤል ሲቀበሉ ነበር፤ አሁን ላይ ግን የሚያጋጥሙ ስህተቶችን ለማረም እንዲቻል የተፈታኞች መረጃ ኦንላይን ላይ እንዲቀመጥ እየተሠራ ነው፡፡
ፈተናውን 250 ሺህ ለሚደርሱ ተማሪዎች ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፈተናውን የሚወስዱ ተማሪዎች ዝርዝር በትምህርት እና ሥልጠና ባለሥልጣን ተረጋግጦ ነው ወደ ሚኒስቴሩ የሚላከው ብለዋል፡፡ በግል ተመዝግበው ፈተናውን በድጋሚ የሚወስዱ ተማሪዎች ምዝገባም በቀጣይነት የሚከናወን በመኾኑ አሁን ላይ ትክክለኛ ቁጥሩን ማስቀመጥ ያስቸግራል ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን ለፈተና ዝግጁ እንዲኾኑ ከማድረግ ጀምሮ አስፈላጊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማጠናቀቃቸውን ገልጸው፤ በመብራት መቆራረጥ ምክንያት ፈተናው ላይ እክል እንዳያጋጥም ጄኔሬተር ጭምር ስለመዘጋጀቱም ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ጊዜ 114 የሚሆኑ ተማሪዎች ተንቀሳቃሽ ስልክ ይዘው በመግባታቸው ውጤታቸው መሰረዙን አስታውሰው፤ ፈተናው ላይ ሞባይል ይዞ የሚመጣ እና መታወቂያ ሳይዝ የሚመጣ ተማሪ ፈተናውን መውሰድ እንደማይችል ጠቅሰዋል። በመሆኑም ተማሪዎች ይህን አውቀው ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ በቀጣይ ጊዜያት ፈተናው በካሜራ እና በጣት አሻራ ታግዞ እንዲሰጥ እቅድ መኖሩንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የካቲት ላይ በተሰጠው ፈተና የአንድ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ወደ ሌላ ዩኒቨርሲቲ ሄደው ምልከታ እንዲያከናውኑ መደረጉን አስታውሰው፤ በቀጣይ በሚሰጠው ፈተና የአንድ ተቋም መምህራን ወደ ሌላ ተቋም ሄደው ፈተና እንዲሰጡ ለማድረግ እየተሠራ ነው ሲሉም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አብራርተዋል፡፡
በመጀመሪያው የመውጫ ፈተና ከተፈታኞች 40 በመቶው ፈተናውን ማለፋቸውን አስታውሰው፤ ተፈታኞች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ በዩኒቨርሲቲዎች በኩል የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን አመላክተዋል፡፡ በቀጣይ ጊዜያት እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ ምን ያህል ተማሪዎችን እንዳስፈተነ እና ምን ያህል ውጤት እንዳስመዘገበ የሚያሳይ መረጃ ይፋ እንደሚደረግም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!