
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ለ2 ሺህ ዓመታት ያህል የተደጋገመ የወረራ ሙከራ እንደተደረገባት የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። በአውሮፓ፣ በእስያ እና በአፍሪካ የተነሱ መንግሥታት ግዛታቸውን ሲያስፋፉ በነበሩበት ጊዜ ኢትዮጵያንም ለማስገበር ብዙ ጊዜ ሞክረዋል።
ከቀደምቶቹ መካከል ደግሞ በግሪክ ንጉሥ የነበረው “ታላቁ አሌክሳንደር” እየተባለ የሚጠራው ንጉስ ተጠቃሽ ነው። ንጉሱ ግዛቱን በማስፋፋት እስከ ግብጽ እና ሕንድ ድረስ አስገብሯል። ከግብጽም አልፎ ኢትዮጵያንም ለመውረር አቅዶ እንደነበር ይነገራል። ይሁን እንጅ ስለኢትዮጵያውያን ጀግንነት ቀድሞ ሰምቶ ስለነበር ጦርነቱን ደፍሮ ለማካሄድ አልደፈረም። ንጉሱ ስለኢትዮጵያውን የተነገረው ጀግንነት እውነት ስላልመሰለው ከሌሎች ምርጥ ከሚባሉ የጦር አለቆች ጋር በመኾን ተራ ሰው በመምሰል ለስለላ ወደ ኢትዮጵያ ገቡ።
ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን የሰማችው የወቅቱ የኢትዮጵያ ንግሥት ሕንደኬም ወደ ቤተ መንግሥት አስጠርታ “ዓለምን አንቀጥቅጠህ የገዛህ ታላቁ እስክንድር ኾይ ዛሬ በሴት እጅ ተይዘሃል” ስትለው ደንግጦ ጥበቧን በማድነቅ፣ ሕዝቡም በጦር የማይፈታ መኾኑን ተናግሯል። ኢትዮጵያን ለማስገበር ከተነሱ የአውሮፓ ነገሥታት መካከል ሌላው የሚጠቀሰው የሮማው አውጉስቶስ ቄሳር ነው። አውግሥቶስ ቄሣር በአውሮፓ፣ በአፍሪካ እና ኤዥያ የሚገኙ በርካታ ሀገራትን ተቆጣጥሮ ከአስገበረ በኋላ “አይሎስ ጋሎስ” በሚባል የጦር አዛዥ የሚመራ 10 ሺህ እግረኛ እና 8 ሺህ ፈረሰኛ ጦር በግብጽ እና በሱዳን በኩል አድርጎ የአክሱምን መንግሥት ለመውጋት ገሰገሰ።
ይህንን የሰሙ ኢትዮጵያውያን ቀድመው ተዘጋጅተው ወደ ኢትዮጵያ ሳይገባ ጦርነት ገጠሙት። ለዓመታት በቆየው ውጊያ የቄሳሩ ጦር እየተመናመነ በመምጣቱ የጦር አዛዡ ከሮማው ንጉስ በታዘዘው መሠረት ጦርነቱ በእርቅ አልቆ የተረፈውን ወደ ሀገሩ ይዞ ተመለሰ። እንግዲህ የጣሊያን ትንኮሳ በዋናነት ከዚህ የጀመረ ይመስላል።
በአውጉስቶስ ቄሳር የደረሰውን ሽንፈት ብድር ለመመለስ በ54 ዓ.ም በሮማ ነግሶ የነበረው ንጉስ ኔሮ ፎክሮ ተነሳ። የኔሮ አማካሪዎችም ኢትዮጵያውያን በጦርነት የማይሸነፉ መኾናቸውን ነገሩት። ወደ ኢትዮጵያ ጦር መላክም ትርፉ ውርደት መኾኑን አስጠነቀቁት። ኔሮ የአማካሪዎቹን ምክር ቢሰማም የዘመኑን የኢትዮጵያ ጦር የሚሰልል ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ላከ። “ኔሮ የአባቶቹን ምኞት ለመፈጸም የዓባይን ምንጭ የሚፈልጉ ናቸው ብሎ ለኢትዮጵያ ንጉሥ ደብዳቤ ጽፎ ሰላዮቹን ወደ ኢትዮጵያ ላከን። የተላክነው ሰላዮች ኢትዮጵያ ውስጥ ከርመን ስንመለስ ሕዝቡ ጦረኛ መኾኑን እና ወደ ኢትዮጵያ ጦር መላክ እንደማያዋጣ ነገርነው። ሀገሪቱ ግን እጅግ ለም ናት አልነው” ሲል ከስለላ ቡድኑ ጋር አብሮ የነበረው “ሴኔካ” የተባለው የታሪክ ጸሐፊ ማስፈሩ ይነገራል።
የተነገረውን አልሰማ ያለው ኔሮ ኢትዮጵያን የማስገበር ምኞት እንደሚችል ተማምኖ “ካምቤይስ” በሚባል የጦር መሪ የሚመራ ጦር ወደ ኢትዮጵያ ልኮ ድል ተመትቶ መመለሱን የታሪክ ጸሃፊዎቹን “ዲዩ ካሲዮ” እና “ፕሊኒ” ን ጠቅሰው ጳውሎስ ኞኞ የኢትዮጵያ እና የኢጣሊያ ጦርነት በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሐፍ አስፍረውታል።
በ19 ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀራመት ስምምነት ላይ የደረሱበት ወቅት ነበር። በዚህ ወቅም ጣሊያኖች ሀገራቸውን ወደ ጥንቱ የሮማ አገዛዝ ለመመለስ ተነሱ። ኢጣሊያ ህልሟን ለማሳካት የተሻለ እና ምቹ ኾኖ ያገኘችው ደግሞ ከቀይ ባሕር – ሕንድ ውቅያኖስ እስከ ዛንዚባር ድረስ ያለው አካባቢ ነው።
በአያቶቻቸው ያልተሳካውን ኢትዮጵያን የማስገበር ሕልም ለማሳካት በሃይማኖት ሰበብ በአባ ጁሴፔ ሳፔቴ አማካይነት ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ከአሰብ ባላባቶች ጋር ተወዳጁ። በ1862 ዓ.ም ከባላባቶቹ “ለማረፊያ” በሚል መሬት በመግዛት “ሩባቲኖ” የሚባል የኢጣሊያ የመርከብ ኩባንያ ወደብ እንዲመሠርት አደረጉ። በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉስ የነበሩት አጤ ተክለጊዮርጊስ ከአጤ ቴዎድሮስ ያልተረጋጋች ሀገር ተረክበው ስለነበር ጉዳዩን ያሰቡበት አይመስልም።
ኩባንያው አሰብን ለ12 ዓመታት ከተጠቀመበት በኋላ በ1874 ዓ.ም (በአጤ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት) ለኢጣሊያ መንግሥት ሸጠው። በዚሁ ዓመት የኢጣሊያ መንግሥት አሰብ የኢጣሊያ ግዛት መኾኑን በአዋጅ አሳወቀ። ከዚህም ባለፈ በምጽዋ ጦር በማስፈር ወደ መሃል ሀገር መስፋፋቱን ቀጠለ።
በሁለቱ ሀገራት መካከል መካረሩ እየጠነከረ ሂዶ ዶጋሌ ላይ ድል ተመቱ። በ1888 የሀገሪቱን ድንበር ጥሶ በድጋሜ ወረራ ፈጸመ። ኢትዮጵያውያንም በጀግንነት በመፋለም በድል አጠናቀቁ። ድሉ ከኢጣሊያ መንግሥት ባለፈ የአውሮፓ መንግሥታትን ጭምር ጭንቀት ውስጥ ከተተ። ሽንፈቱ የነጭ ሽንፈት እንደኾነ ተገነዘቡ።
ድሉን ተከትሎ “ኢትዮጵያ የግዛት ማስፋፋት ልታስብ ትችላለች” በሚል የብዙ ቅኝ ገዥ ሀገራትን ትኩረት መሳብ ቻለ። በሰሜን እና በደቡብ ምስራቅ ጣሊያን፣ በደቡብ ምዕራብ እንግሊዝ እንዲሁም በምስራቅ ፈረንሳይ ከበባ ማድረጉን ቀጠሉ። በተለይም ደግሞ ጣሊያን በአድዋ የገጠማትን የሽንፈትን ቁስል በድል ለመሻር ሀገሪቱን ለመምራት ወደ ስልጣን የመጡት ሁሉ እንቅልፍ ነሳቸው። በ1922 ወደ ስልጣን የመጣው ፋሽስቱ ሞሶሎኒ እረፍት አልነበረውም።
በ1927 ዓ.ም ኢጣሊያ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1908 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገውን የወሰን ስምምነት በማፍረስ 96 ኪሎ ሜትር የኢትዮጵያ ግዛት ላይ በሚገኘው ዋርዴር እና ወልወል ላይ ጦሯን አሰፈረች። ሳትውል ሳታድር በአካባቢው በነበረው በኢትዮጵያ ጦር ላይ ጦርነት ከፈተች። ከዚህም ባለፈ የጣሊያን ጦር መስከረም/1928 የመረብን ወንዝ ተሻግሮ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ጭምር ወረራ ፈጸመ።
የኢትዮጵያውያ አርበኞች ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እስከ አፍንጫው የታጠቀውን የጣሊያን ጦር እረፍት አሳጡት። ትግሉ ከአምስት ዓመታት ቆይታ በኋላ የኢትዮጵያ አርበኞች በከፈሉት መስዋዕትነት በድጋሜ ድል ማድረግ ተችሏል፡፡ ቀኑ የኢትዮጵያ አርበኞች በአንድነት በፋሽስቱ ጣሊያን ዳግም ወረራ ወቅት የከፈሉትን መስዋዕትነት እና ያስገኙትን ድል ለማሰብ በየዓመቱ ሚያዝያ 27 ቀን ይከበራል፡፡
ለዛሬው የኢጣሊያንን ተደጋጋሚ ወረራ አነሳን እንጅ ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ቱርኮች፣ ግብጾች፣ ማህዲስቶች፣ በጎረቤቶቿ ጭምር የተቃጣባትን ትንኮሶ በተባበረ የኢትዮጵያውያን ክንድ ድል በማድረግ ነጻነቷን ያስጠበቀች ቀደምት ሀገር ያደርጋታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!