ሲልቪያ ፓንክረስት – እንግሊዛዊቷ የኢትዮጵያ ጀግና!

46

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሲልቪያ ፓንክረስት እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ሚያዝያ 1882 በሀገረ እንግሊዝ ማንቸስተር ከተማ ውስጥ ነው የተወለዱት። እኝህ እንግሊዛዊት የኢትዮጵያ ጀግና እናታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሴቶች መብት ታጋይ እንደነበሩ “ዕውቀት” የተሰኘው ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡

ሲልቪያ ፓንክረስት ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ የተለያዩ የመገናኛ አውታሮችን በመጠቀም አምርረው መቃወማቸው ተዘግቧል፡፡ ጣሊያን እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ታኅሣስ 05/1934 ወልወል ላይ የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ ፀረ ፋሺስት አቋማቸውን አጠናክረው ቀጠሉ፡፡
ወረራው እየሰፋ ግፍ እና በደሉ ሞልቶ በፈሰሰበት ከ1935 እስከ 1940 ጣሊያን ኢትዮጵያን በተቆጣጠረችበት ዘመን ሲልቪያ ፓንክረስት ያላቋረጠ ተቃውሞ አከናውነዋል፡፡ ብዙ ምሁራንን፣ የሰብዓዊ መብት ደጋፊዎችን፣ የፓርላማ አባላትን እና የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን በማሥተባበር ብዙ አቤቱታዎችን በማሰራጨት እና ሕዝባዊ ስብሰባዎችን በማከናወን የእንግሊዝን መንግሥት ፖሊሲ ለማስቀየር ሞክረዋል፡፡

እንግሊዛዊቷ የኢትዮጵያ ጀግና ሀገራችን የፋሺዝም ሰለባ ከኾነችበት ጊዜ አንስቶ ስለ ኢትዮጵያ ‘የሚናገርና’ የፋሺስት ጣሊያን ወረራን የሚያወግዝ “ዘ ኒው ታይምስ ኤንድ ኢትዮጵያ” የተሰኘ ጋዜጣ በተከታታይ በማሳተም ሰላም ወዳድ አርበኞችን በዓለም ዙሪያ አነቃቅተዋል፤ አነሳስተዋልም፡፡
ኢትዮጵያ ኦን ዘ ኢቭ መጽሐፍ እንዳተተው ሲልቪያ ፓንከርስት የሞሶሎኒ ዓላማ ኢትዮጵያን በሙሉ መውረር መኾኑን ተገነዝበው ሰላም ወዳዱን የዓለም ሕዝብ በጣልያን መንግሥት ላይ ተቃውሞ እንዲያነሳ አድርገዋልም፡፡

በጊዜው የነበረው የመንግሥታቱ ማኅበር “ሊግ አፍ ኔሽን” (The League of Nations) ኢትዮጵያን በጣሊያን ወራሪ ኃይል ከመበላት እንዲያድናት በርካታ ደብዳቤዎችን ጽፈዋል፡፡ ሕዝባዊ ስብሰባዎች እንዲደረጉ ሁኔታዎችን በማመቻቸትም የጣሊያን ሴራ እንዲጋለጥ አድርገዋል፡፡ የታሪክ መምህር ተመስገን ጸጋው እንዳብራሩት ኢትዮጵያ በወቅቱ የመንግሥታቱ ማኅበር አባል ሀገር ነበረች፡፡ ከማኅበሩ ሚና እና ኀላፊነት መካከል ደግሞ ዓለም አቀፍ ግጭቶችን መከላከል እና ደኅንነትን ማሻሻል የሚሉት ይገኙበታል ብለዋል፡፡

ሊጉ በአባል ሀገራት መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን የማስታረቅ እና የመፍትሔ ሃሳቦችን የማቅረብ ሥልጣን ነበረው። ይሁን እንጂ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ተጨማሪ ግጭቶችን መከላከል አለመቻሉና ጣሊያን ኢትዮጵያን መውረሯ ድክመቱ ነው ብለዋል፡፡ ማኅበሩ “የጋራ ደኅንነት” የሚባል ጽንሰ ሃሳብ አለው ያሉት መምህር ተመስገን ይህም በአንድ አባል ሀገር ላይ የሚፈጸም ጥቃት “የሁሉም ሀገር ጥቃት ነው” የሚል መርሕ ነበረው፡፡

በዚህ እሳቤ መሰረት ሊግ ኦፍ ኔሽን ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ ወደ ተግባር መግባት ተስኖታል፤ ሲልቪያ ፓንክረስት ወዲህ ድክመቱን እየተናገሩ ወዲያ ደግሞ ዓለም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እንዲቆም ድምጻቸውን አሰምተዋል ብለዋል፡፡ ሲልቪያ ፓንከርስት የሊግ ኦፍ ኔሽን ጽንሰ ሃሳብን በማስታዎስ ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር በተንቀሳቀሰችበት ጊዜ የመንግሥታቱ ማኅበር በጋራ ደኅንነት ግዴታው መሠረት ኢትዮጵያን እንዲደግፍ እና ፋሺስቱን እንዲወጋ በድፍረት ጠይቀዋል ነው ያሉት፡፡

“’የአውሮፓ ሕሊና ሞቷል ወይ?፤ በእንግሊዝ ሀገር ታማኝ አስተሳስብ ጠፋ ወይ?’ እያሉ ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ የዓለምን ሕዝብ ስሜት ለመቀስቀስ ሞክረው ነበር” በማለት መምህሩ አብራርተዋል፡፡ ጀግናዋ ሴት ፋሺስት ጣሊያንን በእንቁላሉ መቅጣት ካልተቻለ ፋሺዝም ለዓለም ሀገራት እቡይ እንደሚኾን ተናግረው ነበር፡፡ “የፈሩት ይደርሳል፤ የጠሉት ይነግሳል” እንዲሉ ጣሊያንን ሀይ! ባይ በመጥፋቱ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በየካቲት 1937 በአዲስ አበባ ብቻ 30 ሺህ ሕዝብ ተጨፈጨፈ፤ ይህን ሰው በላነቱን ለዓለም ሕዝብ ገላልጠው ያሳዩት ሲልቪያ ፓንክረስት መኾናቸውን በርካታ የታሪክ መጻሕፍት አስፍርዋል፡፡

ሲልቪያ ፓንክረስት ከኢትዮጵያ ባለፈ ለአፍሪካ ሀገራት ዘላቂ ጥቅም በማሰብ በፀረ ፋሺስት እና በፀረ ኮሎኒያሊስት መርሕ ተሰማርተው የነበሩትን በኬንያ እነጆሞ ኬንያታን፣ በጃማይካ እነኤሚ አሽዉድ ጋርቪ እንዲሁም የሞሶሎኒ ተቃዋሚ የነበሩ ጣሊያናዊ ታጋዮችን ጭምር በኢትዮጵያ ጉዳይ እንዲተባበሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በፈረንጆች አቆጣጠር ከ1935 እስከ 1941 በጣሊያን በተወረረችበት ዘመን ሲልቪያ ፓንክረስት የሕይወት ዓላማ እና ተግባር ያደረጉት ኢትዮጵያን ነጻ ማውጣት ነበር፡፡ ባከናወኑት ያላሰለሰ የፖለቲካ ትግልም እንግሊዞች የኢትዮጵያን አርበኞች ጦር እንዲደግፉ አደረጉ፡፡ የጣሊያን ጦርም ድል ተመታ፡፡ የኢትዮጵያ ነጻነትም ተበሰረ፡፡

ሲልቪያ ፓንክረስት በርካታ ምሥጉን ተግባራትንም አከናውነዋል፡፡ ለአብነት “አዲስ ዘመን እና የኢትዮጵያ ዜና” የተሰኘ ጋዜጣ እንዲሁም “ኢትዮጵያ ኦብዘርቨር” የተባለ መጽሔት በማሳተም ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ ዓለም ግንዛቤ እንዲኖረውም አድርገዋል፡፡ ሲልቪያ ከጻፏቸው ሃያ መጻሕፍት መካከል ስምንቱ በኢትዮጵያ ዙሪያ ያተኮሩ ናቸው፡፡

ፋሺስት ጣሊያን በኢትዮጵያውያን አርበኞች ጽኑ ትግል ተሸንፎ የኢትዮጵያ ነጻነት ከተመለሰ ወዲህ ሲልቪያ ፓንክረስት ኑሯቸውን በቋሚነት አዲስ አበባ ውስጥ አድርገው ስለኢትዮጵያ በርካታ ሥራዎችን አከናውነዋል፡፡ ሲልቪያ ፓንክረስት በተወለዱ 79 ዓመታቸው የመስቀል ዕለት እንደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር መሥከረም 17/1960 አዲስ አበባ ውስጥ አረፉ። ቀብራቸውም ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ ከፍተኛ ባልሥልጣናት እና የውጭ ሀገራት ልዑካን በተገኙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል። “ሞት አይቀርም፤ ስም አይቀበርም” እንዲሉ ሲልቪያ ፓንክረስት በሠሩት መልካም ሥራ ሥማቸው ከመቃብር በላይ ውሎ ሁሌም በጀግንነት ሲዘከሩ ይኖራሉ፡፡

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ወራሪው ተደመሰሰ፤ ዙፋኑም ተመለሰ”
Next articleየአልደፈርባይነት ተጋድሎ!