
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በግፍ የመጣ ጠላት በክንድ ተመለሰ፣ በድንፋታ የመጣ ወራሪ በጀግኖቹ ሀገር ተደመሰሰ፣ ሸልሎ መጥቶ አለቀሰ። አንድነት በደማቸው፣ ጀግንነት በጥንተ ባሕሪያቸው፣ አልሸነፍ ባይነት በዘራቸው፣ ድል ማድረግ በታሪካቸው፣ ነፃነትን ማጽናት በክንዳቸው የወረሱ ጀግኖች አያቱ፣ ቅድመ አያቱ እና አባቱ ባፈሩበት ምድር ልጁንም አሳፈሩት። በጥይት አረር ቆልተው የመጣበትን ጎዳና አስጠፉት። በተወደደች ሀገራቸው በሳንጃ ወግተው፣ በጎራዴ ሸልተው አሰናበቱት።
ጀግኖች ናቸውና አባታቸው ድል በመታበት ስፍራ ልጆቹ ድል ይመታሉ፣ አባታቸው የሰጣቸውን ቃል ኪዳን ያጠብቃሉ፣ ይጠብቃሉ፣ ከሠንደቅ በፊት ለመውደቅ ይቀዳደማሉ፣ ሀገር አስቀድሞ ለማለፍ ይፋጠናሉ። በከበረች ደማቸው ሀገር ያጸናሉ፣ በከበረች አጥንታቸው ዙፋን ያረጋሉ፣ ለጠላት በማይፈታ ጀግንነታቸው ነፃነትን በአለት ላይ ያንጻሉ፣ ሉዓላዊነትን፣ የሀገር ዳር ድንበርን በእሳት አጥር ያጥራሉ። የእሳት አጥሩን እጥሳለሁ፣ የሀገርን ዳር ድንበር እደፍራለሁ፣ ነፃነትን ቀምቼ በባርነት አኖራለሁ የሚል ጠላት በመጣ ጊዜ የእሳት ላንቃቸውን ይተፋሉ፣ ነዲድ የሚተፋውን ጎደራዴያቸውን በጠላት አንገት ላይ ያፈልቃሉ፣ ትንታግ የሚረጨውን ጦራቸውን በጠላት ደረት ላይ ይተክላሉ፣ የማይስተው አፈሙዛቸውን ከጠላት ግንባር ላይ ያነጣጥራሉ።
በታላቅ ጀግንነት፣ ባልተደፈረ ነፃነት፣ በጠላት በሚፈራ ሉዓላዊነት የቆዬች ሀገር ከውጭ ወረራ ገጠማት። አንትኩኝ እንጂ ልንካችሁ የማትለው፣ የሰው የማትነካው የራሷንም የማታስነካው ታላቅ ሀገር ወረራዎች ሊወጧት መጡባት። አስቀድሞ ገና በአባ ዳኛው ምኒልክ ዘመን በኢጣልያ የተቃጣባትን ወረራ ወራሪዎችን ባስደነገጠ ጀግንነት ድል መትታ ነበር። ወራሪዎቿ ግን ተሸነፍን ብለው፣ አንገታቸውን ደፍተው፣ አጅቻቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም። ለአርባ ዓመታት ተዘጋጅተው፣ የጣሉትን ክብር ሊያነሱ፣ በዱር በገደል የቀሩ ወገኖቻቸውን ሊክሱ፣ በዓለም ፊት ያፈሩበትን ሽንፈት ሊያካክሱ ዳግም መጡ።
በዚህ ዘመን ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በዙፋን ላይ ተቀምጠው ነበር። ግርማዊነታቸው የሀገራቸውን ሉዓላዊነት አስከብረው፣ ሕዝባቸውን በስልጣኔ ከፍ ከፍ ለማድረግ ደፋ ቀና ላይ ነበሩ። ኢጣልያ ግን በእርሳቸው ዘመን፣ በእርሳቸው ሀገር ለዳግም ወረራ መጣ። ጃንሆይ እጃቸውን ለሰላም ዘረጉ። ዓለም እንዲሰማላቸው፣ በደላቸውን እንዲያውቅላቸው ጠየቁ። ሰሚ ግን አልነበራቸውም። ሞሶሎኒ የሚመራት ሀገር አሻፈረኝ ብላ በኢትዮጵያ ላይ ጦር አነሳች። ለሰላም የዘረጉት እጅ እንደ ፍርሃት የተቆጠረባቸው ጃንሆይ እንደ አባቶቻቸው ሁሉ ጦር ሰብቀው ወደ ጦር ሜዳ አቀኑ።
እንደ ንጉሥ ሳይኾን እንደ እግረኛ ወታደር ተዋጉ። ዳሩ የድል ጀምበር በአጭር ጊዜ አልዘለቀችላቸውም ነበር። አጼ ኃይለ ሥላሴ ወደ ውጭ ሀገራት ሄደው አቤቱታ ለማቅረብ እና በሀገራቸው ላይ የተነሳውን ጠላት ድል ለመምታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ለመምከር ወደ ውጭ እንዲሄዱ ተመከረ።
ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ሕይወቴ እና የኢትዮጵያ እርምጃ በተሰኘው መጽሐፋቸው ወደ ውጭ የሄዱበትን አጋጣሚ ስጽፉ ወደ ዋና ከተማችን ከተመለሰን በኋላ ሚኒስትሮቹ እና መኳንንቱ፣ ታላላቆቹም ሰዎች ሁሉ በቤተመንግሥታችን ተሰባስበው ታላቅ ምክር ተደረገ። በምክሩም ላይ ንጉሠ ነገሥቱ ወደ አውሮፓ ሄደው ኢጣልያ የሰራችብንን ግፍ ሁሉ በቃላቸው ለዓለም መንግሥታት ማኅበር ቢያመለክቱ መልካም ነው ተብሎ ከተቆረጠ በኋላ ለእኛ የሚያስፈልገን ከሁለቱ አንዱን መምረጥ እና መቁረጥ ብቻ ኾነ።
አንደኛው መዋጋትን ትቶ በምክር እንደተቆረጠው ለዓለም መንግሥታት ማኅበር ለማስተዋወቅ ወደ ጄኔቭ መሄድ። ሁለተኛው በከተማ የተገኙትን ጥቂቶች ወታደሮች ይዘን የሽማግሌውን፣ የሴቱንና የሕጻኑን ሞት፣ የከተማዋን መቃጠል ሳናስብ መዋጋት ነው። ከሚያስጨንቅ ሀሳብ በኋላ ወደ ውጭ መሄድ የሚለውን ሀሳብ ተቀበልነው ብለው ጽፈዋል።
ጃንሆይ እደተባለው ሁሉ ወደ ውጭ ሄዱ። በዚህም ጊዜ ደጋጎቹ፣ ጀግኖቹ፣ ልበ ኩሩዎቹ፣ ንጉሣችንን አጣን፣ ክብራችን ተነጠቅን እያሉ አዝነዋል፣ ተክዘዋል። ነገር ግን ሀገራቸውን ለጠላት ላለማስደፈር፣ ለንጉሣቸው እና ለሀገራቸው ታምነው ንጉሣቸውን በአጭር ጊዜ ለመመለስ በጀግንነት ለመዋጋት ቃል ኪዳን አሠሩ። ቃላቸውን የማያጥፉት ጀግኖች ጠላትን እንደ እሳት ይፈጁት ጀመር። ንጉሠ ነገሥት አጼ ኃይለሥላሴ በውጭ ሀገር ኾነው የኢትዮጵያን እውነት ለዓለም እየነገሩ፣ አርበኞችንም እያበረቱ በዚያው ቆዩ። በኢትዮጵያ ምድር ጠላት ሳይጨነቅበት፣ በጥይት አረር ሳይቆላበት የዋለበት ቀን አልነበረም። በንጉሣቸው አበረታችነት፣ በአርበኞች ጀግንነት ድሉ ወደ ተለመደው ወደኢትዮጵያ አዘነበለ። ጃንሆይም ወደ ዙፋናቸው ለመመለስ ተነሱ።
በሪሁን ከበደ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ታሪክ በተሠኘው መጽሐፋቸው ስለ ጃንሆይ መልስ ሲጽፉ ግርማዊ ቀደማዊ ኃይለ ሥላሴ 12 ቀን 1933 ዓ.ም ኦሜድላ ገቡ ብለዋል። ከዚያ በፊት መኖሪያቸው በአውሮፓ ነበር። ከናፈቃቸው እና ከናፈቁት ሕዝባቸው ጋር ይገናኛሉ ዘንድ ጓጉተዋል። በዚሁ ሥፍራ ደም የሚፈስስላት፣ አጥንት የሚከሰከስላት፣ ትወልድ ከትውልድ ጋር በጽኑ መንፈስ የሚገናኝባት የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ በንጉሠ ነገሥቱ እጅ በኦሜድላ በክብር ከፍ ብላ ተሰቀለች።
ጃንሆይ ከኦሜድላ ተነስተው ገሰገሱ። በልያም ደረሱ። ከበልያ ተነስተው ጠላትን እየመቱ፣ አርበኞች እጅ እየነሱላላቸው፣ ንጉሣቸውን ይዘው ጠላትን እየደመመሱ ወደፊት አቀኑ። የሀገሬው ሰውም በደስታ ተቀበላቸው። ጃንሆይ በድል አድራጊነት በመጋቢት 28 ቀን 1933 ዓ.ም እሑድ ደብረ ማርቆስ ገቡ። ከደብረማርቆስ እስከ ወንቃ ድረስ ሕዝቡ በግራና በቀኝ በብዛት ተሠልፎ ወንዱ በሆታ፣ ሴቱ በእልልታ በታላቅ ደስታ ተቀበላቸው።
ጳውሎስ ኞኞ የኢትዮጵያ እና የኢጣልያ ጦርነት በተሰኘው መጽሐፋቸው አርበኞች ጠላትን ድል እየመቱ አዲስ አበባ ሲቃረቡ በኢጣልያ በኩል የነበረውን ጭንቅ ደቡብ አፍሪካዊውን ኢሪክ ሮሲንታልን ጠቅሰው ሲጽፉ ” አርበኞች አዲስ አበባ ሲገቡ በሠይፍ እንደሚያርዷቸውና ቤታቸውንም እንደሚያቃጥሉባቸው እያሰቡ ኢጣልያኖች ፍፁም በኾነ ፍርሃት ተውጠዋል። በየቦታው ምሽጎች ተሠርተዋል። ከተማዋ በሾሃማ ሽቦ ዙሪያዋን ታጥራለች። የመንግሥት ሕንፃዎች እና ጠቃሚ የኾኑ ድርጅቶች ሁሉ በሽቦ ታጥረዋል። አንዳንድ መንገዶችም ሕዝብ እንዳይተላለፍባቸው ተዘግተዋል” ብለዋል። ዳሩ እሾህም መከራም የዙፋን መቀመጫዋን ከተማ በአርበኞች እጅ ከመግባት አላዳናትም።
ጃንኾይ በደብረማርቆስ 25 ቀናት ከሰነበቱ በኋላ ልዑል አልጋ ወራሽ አስፋ ወሰንን፣ ልዕል መኮንን መስፍነ ሐረርን፣ ልዑል ካሳ ኃይሉን፣ ልጅ ዮሐንስ ኢያሱን እና ሌሎችን አስከትለው ሚያዚያ 21 ቀን 1933ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ጀመሩ። ጃንሆይ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ሄዱ። በዚያም የኾነውን ሁሉ አዩ።
በጉዟቸው ለሀገር ፍቅር ሲሉ የተሰዉ ጀግኖች አርበኞችን የሞቱበትን እና የተቀበረቡትን ቦታ እያዩ ገሰገሱ። ከዓመታት በፊት ጃንሆይ ከአዲስ አበባ ወጥተው ሲሄዱ የኢጣልያ ጦር አዲስ አበባ የገባውና የኢጣልያ ሠንደቅ ዓላማ የተሰቀለው ሚያዚያ 27 ቀን ነበር። ከዓመታት በኋላ አጼ ኃይለ ሥላሴ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ጠላት አዲስ አበባ በገባበት ቀን እንዲገቡ ተወስኖ ነበር። እርሳቸውም ሚያዚያ 27 ቀን ፍቼ ተነስተው ጠዋት እንጦጦ ማርያም ደረሱ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!