
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለመላው የኦሮቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። ፕሬዚዳንቱ በመልዕክታቸው የትንሳኤ በዓል በሩሲያ ለዘመናት ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ፣ ሚሊዮኖችን አስተሳስሮ ለበጎ አድራጎት የሚያነሳሳ ቱባ መንፈሳዊ ትውፊት ነው ብለዋል።
የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በአንድ በኩል ታሪካዊ፣ ባሕላዊ እና መንፈሳዊ ቅርሶችን በመጠበቅ፣ የማኅበረሰብ መሠረት የኾነው የቤተሰብ ተቋምን በማጠናከር እና ወጣቶችን በማስተማር፤ በሌላ በኩል መተዛዘንን፣ በጎ አድራጎትን እና ለጎረቤት መልካም መኾንን በመስበክ በኅብረተሰብ ግንባታ የምትጫወተውን ገንቢ ሚና ፕሬዚዳንቱ አውስተዋል።
ካህናት ሁሌም ከሕዝብ ጎን ናቸው፤ ክርስቲያናዊ በጎ አድራጎት ድርጅቶች በፈታኝ ችግሮች ውስጥም ኾነው እገዛ እና ትኩረት ለሚሹ ወገኖች ዛሬም ውጤታማ እና ከራስ ወዳድነት የጸዳ ድጋፍ በመለገስ ላይ ናቸው ብለዋል ፕሬዚዳንት ፑቲን በእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!