“አባቶቻችን በአርበኝነት ተጋድሎ ነፃነቷን አስከብረው ያቆዩልንን ሀገር አፅንተን ማቆየት የሁላችንም ኃላፊነት ነው” ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

22

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 83ኛው የአርበኞች ቀን መታሰቢያ በዓል በአዲስ አበባ አራት ኪሎ የአርበኞች መታሰቢያ ሐውልት በሚገኝበት ስፍራ ተከብሯል፡፡ በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት እና የጥንታዊት ኢትዮጵያ የአርበኞች ማኅበር የበላይ ጠባቂ ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ የጥንት አባቶቻችን በአርበኝነት ተጋድሎ ነፃነቷን አስከብረው ያቆዩልንን ሀገር እና ነፃነት አፅንተን ማቆየት የሁላችንም ኀላፊነት ነው ብለዋል፡፡

ትላንት አባቶቻችን ለኢትዮጵያ ነፃነት ሕይወታቸውን መሥዋእት ከፍለውልናል ያሉት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ አሁን ያለነው ትውልድ ደግሞ የጋራ ጠላታችን የሆነውን ድህነትን በተባበረ ክንዳችን ድል ነስተን የበለፀገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ በትጋት መሥራት አለብን ሲሉ ገልፀዋል።
በክብረ በዓሉ ላይ የኢፌድሪ መከላከያ ሠራዊትን በመወከል የተገኙት የመከላከያ የሰው ሀብት አመራር ዋና መምሪያ ኀላፊ ሌተናል ጀኔራል ሀጫሉ ሸለመ፤ አርበኝነት በትውልድ ቅብብሎሽ የሚቀጥል የኢትዮጵያዊያን መገለጫ እሴት ነው ብለዋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊትም ይህንኑ የጀግኖች አርበኞች እሴትን ተላብሶ ለሃገሩ አንድነትና ሉአላዊነት አኩሪ መሥዋእትነት እየከፈለ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የጥንታዊት ኢትዮጵያ የአርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ በበኩላቸው፤ ዛሬ ላይ እያከበርን ያለው የድል በዓል ትላንት ኢትዮጵያዊያን ለባእዳን ሀገር ላለመገዛት እና የኢትዮጵያን የቀደመ የጀግንነት ታሪክ ጥላሸት ላለማስቀባት የከፈሉት መሥዋእትነት በመሆኑ ትውልዱ ይህን ታሪክ አስቀጥሎ ማለፍ እንዳለበት አሳስበዋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የመከላከያ የሰው ሃብት መምሪያ ኀላፊ ሌተናል ጀኔራል ሀጫሉ ሸለመ እንዲሁም የጥንታዊት ኢትዮጵያ የአርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ የጀግኖች መታሰቢያ ሃውልቱ ላይ የአበባ ጉንጉን ማስቀመጣቸውን ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሕማሙን በመሰለ ሕማም ያለፉት፤ ትንሳኤውን በመሰለ ትንሳኤ ይደምቃሉ!
Next articleየሩሲያው ፕሬዚዳንት የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።