
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያዊያን ክርስቲያኖች በሰሙነ ሕማማት የክርስቶስን ስቃይ፣ መከራ እና ውድ ዋጋ ሁሉ እያሳቡ በመከራ አሳለፉት፡፡ በመከራው መከራውን የመሰሉት ክርስቲያኖች በትንሳኤው ደግሞ ትንሳኤውን መስለው ብቅ አሉ፡፡
ሰሙነ ሕማማት ከሞት በኋላ ዘላለማዊ ሕይዎት፣ ከመከራ ሌሊቶች የሚቀዱ የፍስሃ ጅረቶች፣ ከስደት የሚወረስ ርስት፣ ከበደል የበረታ ይቅርታ እና ፈጽሞ ከመጥፋት ያዳነ አሸናፊነት የተቸረበት የፈተና ወቅት ነው፡፡ ከክር የቀጠነችው የአዳም የመዳን ተስፋ በመጨረሻዋ ስዓት በደም የጸናችበት፤ ሞት ተሸሮ ዘላለማዊ ሕይዎት ተሻግሮ የታየበት ወቅት ነው፡፡
ሰሙነ ሕማማት የመከራ ዳርቻ እና የትንሳኤ ብርሃን መሸጋገሪያ ኾናለች፡፡ በክርስቶስ ክርስቲያን ለሆኑ ኹሉ ሰማይና ምድር፤ ፈጣሪና ፍጡር እርቅ ያወረዱበት፤ ጨለማ በብርሃን የተገለጠበት የይቅርታ እና የሽግግር ሰሞን ናት፡፡ በደል የሌለበት ክርስቶስ ስለሰው ልጅ ፍቅር ሲል ያለበደሉ የተበደለበት ሳምንት ቢኾንም የጨለማን ጽልመት እና የመቃብርን ጉልበት ከመስበር ያገደው ኃይል አልነበረምና፤ እነሆ የክርስቶስ ትንሳኤው ብርሃን ታየ፡፡
ሕማማት የሚለው ቃል ሕመምን፣ ስቃይን፣ መከራን እና ችግርን የሚገልጽ ነው ያሉን የሥነ መለኮት መምሕሩ መጋቢ አሰፋ አይቸው ናቸው፡፡ ሰሙነ ሕማማት ማለት ደግሞ የኢየሩሳሌም ሰዎች “በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው” እያሉ እና ዘንባባ እያነጠፉ በሆሳዕና የተቀበሉትን ክርስቶስን “ይሰቀል፣ ይሰቀል፣ ይሰቀል” እያሉ እስካሰቀሉበት እለተ አርብ ድረስ ያለውን የክርስቶስን ስቃይ፣ መከራ እና ሞት የሚያመላክት ነው ይላሉ፡፡
የክርስቶስን መምጣት አጥብቀው ይጠብቁ የነበሩት አይሁዳውያን ጥበቃቸው የአዳምን በደል በደሙ ክሶ ሰማያዊ ነጻነትን የሚያወርሳቸው እና ከጨለማ የሚያሻግራቸውን ክርስቶስን አልነበረም፡፡ ከዚያ ይልቅ እስራኤላውያንን ከሮማውያን የቅኝ አገዛዝ ነጻ የሚያወጣቸውን ፖለቲካዊ መሲህ ይጠብቁ ነበር፡፡ የጠበቁት መሲህ ዓላማው የጠፋውን የሰውን ልጅ ዋጋ ከፍሎ መመለስ እንጂ አንዱን በሌላው ላይ ማሰልጠን አለመኾኑን ሲረዱ ወንጀለኛው በርባን ተፈትቶ ወንጀል የሌለበት ኢየሱስ እዲሰቀል በጩኸት ጠየቁ፡፡
አይሁዳውያን በዘንባባ ምንጣፍ የተቀበሉት እና በመከራ ብዛት የሸኙት ክርስቶስ እውነተኛ መሲህ እንደነበር ለማወቅ ክቡር ነፍሱ ከክቡር ስጋው እስክትለይ ድረስ ዘግይተዋል፡፡ ነገር የጨለመባቸው እና የእውነተኛውን መሲህ መምጣት የሚጠብቁት ግን በሞቱ ነጻ ወጥተዋል፡፡ የሥነ መለኮት መምህሩ እንደሚሉት ዛሬም በኢትዮጵያ ርሃብን፣ ጦርነትን፣ ስደትን፣ መፈናቀልን፣ መገፋትን እና መገደልን ስናስብ ሰሙነ ሕማማቷ ላይ እንዳለች እንረዳለን፡፡
ትናንት አብረዋት የቆሙት ይሸሻሉ፣ ቃል የገቡት ያብላሉ እንዲኹም የደከመች የሚመስላቸው ጦር ያነሳሉ፤ ነገር ግን ይላሉ መጋቢ አሰፋ ይህ ኹሉ ከመከራ በኋላ የሚመጣውን የኢትዮጵያን ትንሳኤ አያግዱትም፡፡ እንደ መጋቢ አሰፋ ማብራሪያ መቃብርን ፈንቅሎ እና ሞትን በሞቱ ድል አድርጎ የተነሳው ክርስቶስ ያሳደዱትን የሚያሳድድበት እና የበደሉትን የሚበቀልበት ኃይል ነበረው፡፡ ከዚያ ይልቅ የበደሉትን በይቅርታ እና በንስሃ ጠራቸው፡፡
ኢትዮጵያውያንም የኢትዮጵያን ትንሳኤ የሚያዩበት ወቅት ሩቅ አይደለምና አኹን ያለፈ ታሪካቸው፣ የቀደመ በደላቸው እና የጠገገ ቁስላቸውን የሚያስታውሱበት እና ለበቀል የሚነሳሱበት ጊዜ አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ በጋራ ቆመው፣ በፍቅር ተቃቅፈው እና በይቅርታ ተሻግረው የሀገራቸውን ትንሳኤ ሊጠብቁ ይገባል ሲሉ መክረዋል፡፡ ሕማሙን በመሰለ ሕማም ያለፉ ሁሉ ትንሳኤውን በመሰለ ትንሳኤ ይነሳሉ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!