የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎችና አምባሳደሮች ለትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።

21

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች እና አምባሳደሮች ለክርስትና እምነት ተከታዮች ለትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትና የመልካም ምኞት መግለጫ አስተላልፈዋል። በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን፤ የትንሣኤ በዓል ለተቸገሩ ወገኖች መልካም ነገርን የማድረግ ጅማሮ ነው ብለዋል።

ይህም በዜጎች መካከል ሰላም፣ አንድነትና መተባበር እንዲኖር መልካምነት አሸናፊ እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑንም ገልጸዋል። በጋራ በመሆን አንድ የሚያደርጉንን መልካም እሴቶች ለበጎ አላማ በማዋል ችግሮችን ማለፍና ደስታና ብልጽግና ላይ መድረስ እንደሚቻል ተናግረዋል። ለኢትዮጵያውያን ጓደኞቼ፣ ወንድሞቼ እና እህቶቼ በዓሉ የጤና፣ የደስታና የልባችሁ መሻት የሚፈጸምበት እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል አምባሳደሩ በመልዕክታቸው።

በኢትዮጵያ የጅቡቲ አምባሳደር አብዲ መሐሙድ ኢይቤ፤ ለመላው ኢትዮጵያውያን የክርስትና እምነት ተከታዮች የትንሣኤ በዓል የደስታ፣ የሰላምና የፍቅር እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል። በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ኪራ ስሚዝ ሲንድበርግ፤ ለመላው ኢትዮጵያውያን የክርስትና እምነት ተከታዮች የትንሣኤ በዓል የሰላምና የደስታ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን በትዊተር ገጻቸው አስተላልፈዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ በዓሉን አስመልክቶ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባስተላለፈው መልዕክት በዓሉ የሰላምና የደስታ እንዲሆን ተመኝቷል። በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ በበኩሉ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት በዓሉ የሰላምና የፍቅር እንዲሆን መልካም ምኞቱን ገልጿል።

በኢትዮጵያ የዩናይትድ ኪንግደም ኤምባሲ የትንሣኤ በዓል ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የደስታ እንዲሆን ተመኝቷል። በኢትዮጵያ የኢራን እስላሚክ ሪፐብሊክ ኤምባሲም “የኢራን እስላሚክ ሪፐብሊክ ኤምባሲ እና ሠራተኞች ለመላው ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች መልካም የስቅለትና የትንሣኤ በዓል እንዲሆንላችሁ ይመኛሉ፤ መልካም ፋሲካ!” ሲል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቱን አስተላልፏል።

ኢዜአ እንደዘገበው የፓኪስታን፣ የአውስትራሊያ፣ የስዊድን፣ የስዊዘርላንድ፣ የስፔን፣ የብሩንዲና ሌሎችም ኢምባሲዎች የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ማዕድ አጋሩ።
Next articleሕማሙን በመሰለ ሕማም ያለፉት፤ ትንሳኤውን በመሰለ ትንሳኤ ይደምቃሉ!