“ሞት ተረትቷል፤ ክርስቶስም ተነስቷል”

29

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የእናቱን ድንግልና ሳይለውጥ የተጸነሰው፣ በሕቱም ማሕጸን ያደረው፣ የእናቱን ድንግልና ሳይለውጥ የተወለደው፣ በሕቱም መቃብር ተነስቷል፣ ሞት ተረትቷል፣ በኃያሉ ጌታ ድል ተመትቷል። የመግነዝ ጨርቅ ማሰር አልተቻለውም፣ የመቃብር ድንጋይ አላስቀረውም፣ የመቃብር ጠባቂዎች አላስቆሙትም፣ ጦር እና ጋሻቸው፣ ሰይፍ እና ጎራዴያቸው ከመነሳት አላገዱትም። ይልቅ መቃብሩን ሳይከፍት ሲኦልን መዝብሯት፣ በግዞት የያዘቻቸውን ነፍሳት ቀምቷት፣ በሯንም ዘግቷት ሲወጣ የማየት ኃይሉ አልነበራቸውም።

ምድር በብርሃን ተመልታለች፣ ሰማይም አብዝታ ፈክታለች፣ ሞት የማያሸንፈው፣ መቃብር የማይዘው አምላክ ተነስቷልና በኃዘን እና በቅሶ ፋንታ ደስታ በዝታለች። በእለተ አርብ ያለቀሱት በደስታ ተመልተዋል፣ በእለተ አርብ የደነፉት አንገታቸውን ደፍተዋል፣ በስቅለቱ የተደሰቱት፣ የተኩራሩት፣ የዘበቱት፣ በጥፊ የመቱት፣ መራራ ሐሞት ያጠጡት፣ በጦር የወጉት በትንሳኤ ደንግጠዋል፣ በብርሃኑ ርደዋል፣ ተንቀጥቅጠዋል።

ቀበርነው ሲሉ ተነሳባቸው። በመቃብር አስረን አስቀረነው ያሉት በግርማው መጣባቸውና መግቢያው ጨነቃቸው። ሰቀልንልህ ላሉት፣ ገደልንህ ብለው ላሳዩት ሁሉ የሚነግሩት ግራ ገባቸው፣ ከዚያ በፊትም፣ ከዚያ በኋላም እንዲህ አይነት ኃያል አልገጠማቸውምና። በስቅለቱ ያለቀሱት፣ በስቅለቱ ደረታቸውን የደቁት፣ ፊታቸውን የነጩት በትንሳኤው ደስታ በዛላቸው፣ ብርሃን አጥለቀለቃቸው፣ ሀሴት ዋጣቸው። በጌታዋ መሰቀል የደነገጠችው ሰማይ ተደሰተች፣ በጌታዋ መሰቀል የጨለመችው ምድር ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ በብርሃን ተመላች። ሞትን ድል የሚያድርግ፣ በሞቱ ሞትን የሚገድል የማይሸነፍ አምላክ አላቸውና።

ትንሳኤው በፊት በኋላቸው፣ በግራ በቀኛቸው የበዙ ጠባቂዎች ያሏቸውን፣ በምድር ያሉ ጠላቶቻችን እናደቅቃለን፣ ማንም አያስፈራንም፣ አያስደነግጠንም የሚሉ ሹማምንትን አስደንግጧቸዋል፣ ከእኛ በላይ ላሳር ያሉትን የት እንግባ አስብሏቸዋል። ትንሳኤው በጨለማ ውስጥ የነበሩትን በብርሃን መልቷቸዋል። የታሠሩትን ፈትቶ አውጧቸዋል። ኃይል ሰጥቷቸዋል፣ ክብርና ሞገስን አድሏቸዋል። በተስፋ ሲጠብቁት ለነበሩት የልባቸውን መሻት ፈጽሞላቸዋል። ጠላታቸውን ለዘላለም ድል መትቶላቸዋል፣ ጣላታቸውን ለዘላለም አንገት አስደፍቶላቸዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የገደማ ዮርዳኖስ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቤተክርስቲያን የመጻሕፍት ትርጓሜ መምህር መምህር ዘላለም በላይ ክርስቶስ በመቃብር ፈርሶ በስብሶ መቅረትን አሳለፈልን፣ ወደ ሲኦል መውረድንም አሳልፏል፣ እኛ ፋሲካን ስናከብር ከሞት ወደ ሕይወት የተሻሸገርነብት፣ ከሞተ ስጋ ከሞተ ነፍስ የዳንበት ቀን ነው ይላሉ።

መቃብሩን ዘግተውት፣ ጭፍሮች መቃብሩን ከበውት ነበር፣ እርሱ ግን በኃይሉ ተነሳ። የመቃብር ጠባቂዎቹ እንደበደን ኾኑ። ምድርን ብርሃን መላት፣ ምስጋና ተሰማ። ሰው ተኝቶ ከእንቅልፉ እንደሚነሳ ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስም ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ። ክርስቶስ የተቀበረው በአዲስ መቃብር ነው። ክርስቶስ በአዲስ መቃብር መቀበሩም የድሮው መቃብር አልፏል ማለቱ ነው። ክርስቶስ መቃብሩን ድል አድርጎ ተነስቷል።

ክርስቶስ ከተነሳ በኋላ መላእኩ መጣና የመቃብሩን ድንጋይ አንስቶ ተቀመጠበት። ይሄም እግዚአብሔር መርገምን ከሰው ልጅ እንዳራቀ ሲያጠይቅ ነው። ዓለምን በመሀል እጁ የያዘ አምላክ ተነሳ። ክርስቶስ ተነሳ ስንል የተነሳው ለእኛ ነው። የእኛን መነሳት ያስተምረን ዘንድ ተነሳ። ለእርሱማ ሁሉም በእጁ ነው። ለእኛም መነሳት በትንሳኤ ስጋ እና በትንሳኤ ልቡና ይኖር ዘንድ መልካም ነው። ከሁሉም ትንሳኤ ልቡና ይኖር ዘንድ ግድ ይላል ነው የሚሉት። ክፋተኛ የነበረ ሰው ክፋቱን ካልተወ፣ አመጸኛ የነበረ አመጹን ካልተወ በዓል አከበረ አንልም። ትንሳኤን ማክበር በመንፈስ መነሳት ነው፣ ትንሳኤ አዲስ ሕይወት ነው፣ አዲስ ልቡና፣ አዲስ መንፈስ ነው ይላሉ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የአራቱ ጉባዔያት መምህር ሊቀ ሊቃውንት ስመዓኮነ መልአክ በእለተ አርብ ፍቅሩን እንዳየን፣ በእለተ እሁድ ኃይሉን ተመለከትን፣ በእለተ አርብ የተሰቀለው አምላክ፣ በእለተ እሁድ ድል ነስቶ ተነሳ ነው የሚሉት። ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አንጸዋለሁ አላቸው። ስለዚህ አይሁድ ይህ ቤተ መቅደስ ከ46 ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፥ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን? አሉት። እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር። ስለዚህ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ይህን እንደ ተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ። በፋሲካ በዓልም በኢየሩሳሌም ሳለ፥ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ ብዙ ሰዎች በስሙ አመኑ እንደተባለ ቤተመቅደስ ያለው ሰውነቱን ስጋውን ነበር፣ በሦስተኛው ቀን አነሰዋለሁ እንዳለ በሦስተኛው ቀን ተነሳ ይላሉ ሊቁ።

እረኛውን እመታዋለሁ፣ በጎቹም ይበተናሉ እንደተባለ ሐዋርያት በስቅለቱ ተበታትነው ነበር። እርሱ ግን እነሳለሁ ብሏቸው ስለነበር የትንሳኤን ቀን በተስፋ ይጠብቁ ነበር። እነሳለሁ ባለባት ሌሊት ሴቶች አልተኙም። ይልቁንም አብዝታ ትወደው የነበረው ማርያም መግደላዊት በአትክልቱ ስፍራ ታለቅስ ነበር። አብዝታም የወደደችው ብዙ ሐጥያቷ ስለተተወላት ነው። ይሄም የተደደረገላት ሴት እያለቀሰች ጠበቀችው። ዛሬም ቤተ ክርስቲያን ሳትተኛ የጌታን መነሳት ትጠብቀዋለች ነው የሚሉት።

ገና ሌሊት ሳለ ከመቃብር ተነሳ። ክርስቶስ በሌሊት ታላላቅ ሥርዓትን ሠርቷል። ክርስቶስ ዳግም የሚመጣው በመንፈቀ ሌሊት ነው ተብሎ ይታመናል። ዓለም የተፈጠረችው በመንፈቀ ሌሊት ነው፣ የምታልፈውም በመንፈቀ ሌሊት ነው ብለን እናምናለን። በጨለማ ተነስቶ ለእኛ ብርሃን ኾነልን። እርሱ ሲነሳ መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ አላለም። ትንሳኤው ከእነ አላዛር ትንሳኤ ይለያል። አላዛር ከመቃብር ሲወጣ መቃብር እንዲከፈትለት፣ መግነዝ እንዲፈታለት ሰዎቹ ታዝዘዋል። ክርስቶስ ግን በራሱ ስልጣን እንደተነሳ ለማጠየቅ፣ መግነዝም የሚፈታለት፣ መቃብርም የሚከፍትለት ማንም አልነበረም።

እንዲያውም ሲወለድ የእናቱን ማሕተመ ድንግልናዋን እንዳልፈታው ሁሉ ሲነሳም በታተመ መቃብር ነው የወጣው እንጂ መቃብር ተከፍቶ አይደለም። አይሁድም መዘጋቱን አይተው አለመነሳቱን ነው ያመኑት። በሰውነት ሞተ ስንል መለኮት የተለየው ሰውነት አይደለም፣ ድንግል ማርያም የወደለችው መለኮት የተለየው ሰውነት አይደለም፣ ለዚያም ምልክት ይኾን ዘንድ መቃብር ሳይከፍት ተነሳ ይላሉ።

መግነዙን ትቶ ነው የተነሳው። መግነዙ የፍዳ እና የመርገም ምሳሌ ስለኾነ ከዚህ በኋላ ፍዳና መርገም ቀረላችሁ ለማለት ነው። ከተነሳ በኋላ ምን ለበሰ ያሉ እንደኾነ የእርሱ ልብስ ብርሃን ነው። ክርስቶስ ብርሃን ለብሱ ነው። ከትንሳኤ በኋላ ብርሃን መልበስ እንዳለ አሳየን። ሞት የመጣው በሴት በኩል ነበርና ሞት መጥፋቱ የተረጋገጠው በሴት በኩል ነው፣ ትንሳኤውን ንገሩ ብሎ የነገራቸው ለሴቶች ነው። በዓለም ላይ ሴቶች የሞት መልእክተኞች ይባሉ ነበር፣ አሁን ግን ያን ለወጠላቸው፣ አሁን የትንሳኤ መልክተኞች ኾነዋል ነው የሚሉት መምህሩ።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleደብረ ብርሃን – የተስፋዎች መሪ!
Next article83ኛው የአርበኞች ቀን መታሰቢያ በዓል በአዲስ አበባ ተከበረ።