ደብረ ብርሃን – የተስፋዎች መሪ!

93

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ደብረ ኤባን ከስድስት መቶ ዓመታት በፊት አጼ ዘርዓያዕቆብ ቆረቆሯት። በከተማዋ እና በዙሪያዋ የነገሡ ነገሥታት ታላላቅ ታሪኮችን ሠርተው አልፈዋል፡፡ ለታሪክ፣ ለአሥተዳደር፣ ለባሕል እና ለምጣኔ ሃብት መነቃቃትም ጉልህ አበርክቶ ነበራቸው።
አጼ ዘርዓያዕቆብ በዘመነ መንግሥታቸው በሰጡት ትክክለኛ ፍርድ ምክንያት ከሰማይ ብርሃን በመውረዱ ስሟ ከደብረ ኤባ ወደ ደብረ ብርሃን እንደተቀየረም አፈ ታሪክ ይነግረናል።

የዛሬዋ የሰሜን ሸዋ መዲና፣ የአማራ ክልል ፈርጧ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ እንብርቷ፣ ደብረ ብርሃን በተለያዩ ዘመናት ነገሥታት ታላላቅ ሀገራዊ ታሪኮችን ከውነውባታል። የንጉሥ ሣኅለ ሥላሴ ቤተ መንግሥትን ጨምሮ የከተማዋ መሥራች የአጼ ዘርዓያዕቆብ መቀመጫ የነበረች መኾኗ፣ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ከአጼ ዮሐንስ ጋር ስምምነት የፈጸሙበት የልቼ ጥንታዊ ቤተ መንግሥት መገኛነቷ ለታላቅ የፖለቲካ ማዕከልነቷ ማሳያዎች ናቸው። የታሪክ፣ የባሕል፣ የምጣኔ ሃብት መስህብነቷ አሁንም እንዳለ ነው።

ለጤና ተስማሚው ቀዝቃዛው አየሯ፣ ለአካባቢው ከተሞች ያላት ማዕከላዊነት፣ የቅን፣ ታሪክ አዋቂ እና ባሕል አክባሪ ሕዝቦቿ ለኑሮ እና ለልማት ተመራጭ አድርገዋታል።

የተፈጥሮ ፀጋዋ ለአልሚዎች ምቹ መኾን እና ያላት ቀልጣፋ አገልግሎት የባለሃብቶች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን የከተማ አሥተዳደሩ የመሬት መምሪያ ኀላፊ ወይዘሮ እታለማሁ ይምታቱ ለአሚኮ የበኩር ዘጋቢ ተናግረዋል።

ሰፊ ኢንቨስትመንት እያስተናገደች ያለችው ደብረ ብርሃን ከተማ አሁን ላይ 621 አልሚዎች የተመዘገቡባት እና 98ቱ ማምረት የጀመሩ ሲኾን የጂኦሜትሮፖሊታን ከተማ ደረጃነትም አግኝታለች። የሥራ ዕድል በመፍጠርም አበረታች ደረጃ ላይ ትገኛለች። ለኢንዱስትሪ እና ለኢንቨስትመንት 2 ሺህ 50 ሄክታር መሬት ከልላ አልሚዎችን ትጠብቃለች።

በደብረ ብርሃን ለእንጨት፣ ለብረታ ብረት፣ ለጨርቃጨርቅ፣ ለቆዳ፣ ለአልባሳት፣ ለኬሚካል፣ ለግንባታ እንዲሁም ለምግብ እና ለመድኃኒት ማምረቻ ቦታዎች ተዘጋጅተዋል።

ከሰሜን ኢትዮጵያ እስከ ደቡብ የሚያስኬደው አስፓልት እና ሌሎች መንገዶች የሚመግቧት ደብረ ብርሃን ለኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ያላት ቅርበትም ለኑሮ እና ለልማት ያላትን ምቹነት ይጨምረዋል።

በዲጂታል የመሬት አሥተዳደር እና የመረጃ ሥርዓት ለመጠቀም ከፌዴራል ከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር እና ከክልሉ መሰረተ ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር በቀዳሚነት ወደ ሥራ ገብታለች።

የመሬት ዘርፍ አገልግሎትን ከወረቀት ንክኪ ነጻ በማድረግ የመረጃዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ፤ ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠትም ደብረ ብርሃን ዝግጁ ኾናለች።

ታሪካዊዋ እና እድሜ ጠገቧ ደብረ ብርሃን በ1986 ዓ.ም ወደ ከተማ አሥተዳደርነት ያደገች ሲኾን ከ2 ሺህ ዓ.ም ወዲህ መነቃቃቷ ይነገራል። በ2014 ዓ. ም ደግሞ ወደ ሪጂኦፖሊታን ደረጃ አድጋለች፤ ከ400 ሺህ በላይ ሕዝብም አላት።

የመረጃ ምንጭ፦የከተማ አሥተዳደሩ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን እና አሚኮ በኩር ጋዜጣ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጌታችን ተመረመረ ዲያቢሎስ ታሰረ” ብስራት ነጋሪ ካህናት
Next article“ሞት ተረትቷል፤ ክርስቶስም ተነስቷል”