“ጌታችን ተመረመረ ዲያቢሎስ ታሰረ” ብስራት ነጋሪ ካህናት

47

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በክርስቶስ እስትንፋስ የተፈጠረችው ዓለም በደሙ ከዘላለማዊ ሞት ነጻ ወጣች፡፡ የክርስቶስ ስቅላት፣ ሞት እና ትንሣኤ እንደ ውኃ ፈሳሽ ደራሽ አልነበሩምና ለአዳም የተገባለት ቃል አንድም ሳይጎድል ተፈጸመ፡፡ ይህንን ማድረግ ከኢየሱስ ክርስቶስ ውጭ ማን ይችል ነበር?

የሕማማት መጨረሻ በኾነችው “ቅዳም ስዑር” የሃጢያት ውኃ ጎድሎ የጽድቅ ውኃ ደግሞ በክርስቶስ ደምና ሥጋ ዳግም መሙላቱን ለማብሰር ካህናት በጠዋት ቄጤማ ይዘው የሚዞሩበት ዕለት ነው፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት በቀበሌ 16 ደብረ ምህረት ቅድስት ኪዳነ ምኅረት ቤተክርቲያን የስብከተ ወንጌል መምህር በትረወንጌል ካሳ እንዳሉት ዓለም ፈጣሪን ከመበደሉ የተነሳ በፍል ውኃ ተቀጣ። በዚያን ጊዜ ኖህ መርከብ ሰርቶ ልጆቹን፣ የልጅ ሚስቶቹን፣ የእንስሳትን እና የአዕዋፋትን ዘር አተረፈ።

ኖህም መርከቡን ለማሳረፍ ደረቅ ቦታ እንዲፈልጉ አዕዋፋትን ላከ። ቅድሚያ ቁራ ተልኮ ሳይመለስ ቀረ። ቀጥሎ እርግብን ሲልክ በመጀመሪያ አጥታ ተመለሰች። ድጋሜ ተልካ ስትመለስ የጥፋት ውኃው መጉደሉን ለማብሰር በአፏ ቄጤማ ይዛ የተመለሰችበት ዕለት ነው።

የአዲስ ኪዳን ተከታዮችም ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሲል በመስቀሉ ላይ በመዋሉ ከዚህ በኋላ በበደል እንጠፋ የነበረውን ወይም ባሕረ ሲኦል መቅረቱን ለማሳየት አባቶች “ጌታችን ተመረመረ (ተገኘልን) ዲያቢሎስ ታሰረ” እያሉ ብስራት ነጋሪ ካህናት ቄጤማውን ይዘው የምስራቹን ያውጃሉ።

ቅዳሜ ንጉሣዋ በመቃብር ውስጥ አድሯልና ኦሪትን ሽራ ሐዲስን አሃዱ ማለቷን ተከትሎ “ቅዳም ስዑር” ተባለች፡፡ በዚች ዕለት የክርስቶስን መከራ የሚያስቡት ክርስቲያኖች ከወትሮው በተለየ በጾም ያሳልፏታልና “የተሻረችው ቅዳሜ” ሲሉም ይጠሯታል፡፡ ይህች ቅዳሜ “ቅዱስ ቅዳሜ” የሚል ስያሜም አላት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአቶ ይርጋ ሲሳይ የትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት!
Next articleደብረ ብርሃን – የተስፋዎች መሪ!