11 ሰዓት ላይ ከመስቀል ወደ መቃብር የወረደበት ሰዓት ነው፡፡

27

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)አዳምን እና ልጆቹን ከሃጢያት ሊያነጻ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞትን በሞቱ የሻረው ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ነፍሱ ከቅዱስ ስጋው ከተለየች በኋላ ለሁለት ሰዓታት በመስቀል ላይ ቆይቶ ነበር፡፡
በዚህ ሰዓት ምን ኾነ?

ለንጊኖስ የጌታ ወዳጅ ነበር፡፡ አንድ ዐይናም ነበር፡፡ አይሁድ በጌታችን እና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ መከራ ባጸኑበት ወቅት ስላልተባበራቸው ከማኅበራዊ ኑሮ ይለዩኛል ብሎ በጫካ ተደብቆ ዋለ፡፡ ሰዓቱ እልፍ ሲል ወደ ቀራንዮ አደባባይ መጥቶ ነበር፡፡

ለንጊኖስ ወደ ቀራንዮ ለመውጣቱ ምክንያት ደግሞ አሁን አይሁድ ወደ ቤታቸው ሄደው ይኾናል ብሎ አስቦ ነበር፡፡ ነገር ግን አይሁዳውያን መስቀሉ አካባቢ ነበሩ፡፡ ለንጊኖስም ከመስቀሉ ስር በደረሰ ጊዜ ጌታችን ነፍሱ ከሥጋው ተለይቷል፡፡ እሱም ሞቷል፤ አይቀየመኝም ብሎ በፈረስ ላይ ተቀምጦ የኢየሱስ ክርስቶስን ጎኑን በጦር ወጋው፡፡ በዚህ ሰዓት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጎን ትኩስ ደም እና ውኃ ወጣ፡፡ የነጠበው ደምም በለንጊኖስ ዓይን ላይ ባረፈ ጊዜ ዐይኑ በራ ይላሉ በጽርሐአርያም ደብረ ሲና በዓታ ለማርያም አንድነት ገዳም የስብከተ ወንጌል ኀላፊ መምህር አብርሃም ሞላ።

አስራ አንድ ሰዓት በኾነ ጊዜ ኒቆዲሞስ እና ዮሴፍ የአምላካቸውን ቅዱስ ሥጋ ከመስቀል ላይ ማውረድ ፈለጉ፡፡ “ንጉስ የገደለውን አንበሳ የሰበረውን የሚነካ የለምና” ኒቆዲሞስ እና ዮሴፍ የጌታቸውን ቅዱስ ሥጋ ለማውረድ ጲላጦስን ሄደው ለመኑት፤ ፈቀደላቸው፤ አውረዱት፡፡ በአዲስ በፍታ በሚገንዙበት ጊዜ ዝም ብለው ነበርና “እንዴት ዝም ብላችሁ ትገንዙኛላችሁ? በለበስኩት ሥጋ ብሞትም መለኮት አልተለየኝም ቅዱስ ኃያል፣ ቅዱስ እግዚአብሔር፣ ቅዱስ ሕያው ዘእየመውት፤” የማይሰቀለው ተሰቀለ፣ የማይሞተው ሞተ፣ የማይቀበረው ተቀበረ እያላችሁ ገንዙኝ አላቸው፡፡ በለበስኩት ሥጋ ብሞትም መለኮት አልተለየኝም አላቸው እነሱም ቅዱስ ኃያል፣ ቅዱስ እግዚአብሔር፣ ቅዱስ ሕያው ዘእይመውት እያሉ ከፈኑት እና ዮሴፍ እቀበርባታለሁ ብሎ ባዘጋጃት አዲስ መቃብር ቀበሩት ይላሉ መምህሩ፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት ፍቅርን፣ መስዋዕትነትን እና ይቅርባይነትን እንማራለን።
Next articleየጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለ2016 ዓ.ም የትንሣኤ በዓል እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት!