
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የማይሞተው አምላክ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞተ፡፡ ለአዳም እና ለልጆቹ ድኅነት ሲል ሞትን በሞቱ ሊሽር በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞተ፡፡ ዓለምን የፈጠረ የዓለማት አምላክ በአይሁድ እጅ ተይዞ ተገፋ፣ ተዳፋ፣ ተገረፈ፣ መስቀል ተሸክሞ ከጲላጦስ አደባባይ እስከ ቀራንዮ ተሰቃየ፡፡
ቀራንዮ ሲደርስ በተሸከመው መስቀል ላይ ሰቀሉት፡፡ በተሰቀለ ሰዓትም ፀሐይ፣ ጨረቃ እና ከዋከብትም የጌታችን እርቃን አናሳይም ብለው ብርሃናቸውን ከልክለው ነበር ይላሉ በጽርሐአርያም ደብረ ሲና በዓታ ለማርያም አንድነት ገዳም የስብከተ ወንጌል ኀላፊ መምህር አብርሃም ሞላ።
ከጠዋት እስከ ስድስት ሰዓት ብርሃን ነበር፤ ከስድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ግን ጨለማ ኾነ፡፡ ከዘጠኝ ሰዓት እስከ 12 ሰዓት ብርሃን ነበር፡፡ ይህም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሦስት ቀን እና ከሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር ውስጥ እቆያለሁ፤ በሦስተኛው ቀን እነሳለሁ አትፍሩ እያለ ሐዋርያትን ያስተማራቸው ትምህርት ይፈጸም ዘንድ ቀኑ ጨልሞ ነበር ይላሉ መምህሩ፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አርብ ስድስት ሰዓት በመስቀል ላይ ከተሰቀለ በኋላ ታምራት ተፈጽመዋል፡፡ ዘጠኝ ሰዓት ሲኾን ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ስጋው በፈቃዱ ተለይታለች ይላሉ፡፡
ጌታን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ ነፍሱ ሲኦል ወርዳ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በሲኦል የነበሩ ነፍሳትን በርብራ ማርካ ይዞ ወጥታለች፡፡ ሲኦልም ባዶዋን ቀርታ ነበር፡፡ በሥጋው በመቃብር ያሉ ከ500 የሚበልጡ ከ600 የሚያንሱ ሙታን አስነስቷል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክረስቶስ ለአዳም እና ለልጆቹ ድኅነት ሲል ነበር በመሥቀል ላይ የዋለው፡፡ በመስቀል ላይ በነበረ ጊዜ ጥጦስ እና ዳክርስ የሚባሉ ሁለት ቀማኞች በቀኙ እና በግራው ተሰቅለው ነበር፡፡
የደጋው ሲወጣ የቆላው ሲወርድ ተሰቅለው ሲያያቸው እነዚህ እነማን ናቸው ብሎ ይጠይቃል፡፡ በቀኝ የተሰቀለውን “ይኸ ማን ነው?” ብለው ሲጠይቁ ይኸማ ቀማኛ ነው ይላሉ፤ “በግራ የተሰቀለውስ ማን ነው?” ብለው ሲጠይቁ ይኸም ቀማኛ ነው ይላሉ፡፡ በመካከል የተሰቀለውን ክርስቶስን ይህስ ማን ነው ብለው ሲጠይቁ ይህማ የቀማኞች አለቃ ነው ይሏቸዋል፤ እንዲፈርዱበት አስበው ነው በመካካል የሰቀሉት ይላሉ መምህር አብርሃም፡፡
በመካካል ሲሰቅሉት ቀኝ አዝማች ግራ አዝማች ሾምንልህ እያሉም ይሳለቁበት እንደነበር መምህሩ ተናግረዋል፡፡ ፈያታዊ ዘየማን ወይም ጥጦስ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ፣ ከዮሴፍ እና ከሰሎሜ ጋር ወደ ግብጽ በተሰደደ ጊዜ ሃብታቸውን ዘረፏቸው፡፡ ጥጦስ ሲያዩው ህጻኑ አሳዘነውና እነዚኽስ የቤተ መንግሥት ሰዎች ይመስላሉ እንመልስላቸው ብሎ የዘረፏቸውን መለሱላቸው። ሌሎች እንዳይቀሟቸውም ጥጦስ ታቅፎት በረሃውን ሸኟቸው፡፡ በዚህ ሰዓት ከ30 ዓመት በኋላ መስቀል ላይ እንገናኝ ከአዳም ቀድመህ ገነት ትገባለህ ብሎ ነግሮት ነበርና መስቀል ላይ ተገናኙ፡፡ በዚህ ሰዓት “በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” ብሎ ለመነው ጥጦስ ኢየሱስ ክርስቶስን፡፡ ዳክርስ ግን በመስቀል ላይ “ተጨንቆ እያየኸው ትለምነዋልህን” ብሎ ይሳለቅበት ነበር፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም እውነት እውነት እልሃለሁ ከአዳም ቀድመህ ገነት ትገባለህ ብሎ ደመ ማኅተሙን ሰጠው፡፡ ከአዳም ቀድሞ በሱራፌል ከምትጠበቀዋ ገነት ገባ ይላሉ መምህር አብርሃም፡፡
በመጨረሻም በመስቀሉ ሥር ኾና የምታለቅሰውን እናቱን ቅድስት ድንግል ማርያምን ለወልደ ነጎድጓ ቅዱስ ዮሐንስ እነኾ ልጅሽ አላት፤ ለወልደ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስም እነኋት እናትህ ብሎ ከሰጠው በኋላ ነፍሱን ከስጋው ለይቷል ይላሉ መምህር አብርሃም፡፡ መምህር አብርሃም ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉንም ከፈጸመ በኋላ “አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ” ብሎ በለመነ ጊዜ ሌሎች መጥተው እንዲያድኑት እየተጣራ ነው ብለው ተሳለቁበት እርሱ ግን በገዛ ሥልጣኑ ነፍሱን ከስጋው ለየ ብለዋል መምህሩ፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!