
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ ሹመት ማለደ የበዓል ሙክት ለመግዛት ሰቆጣ ገበያ ከተዘዋወሩ በኃላ በ15 ሺህ ብር መሸመታቸውን ነግረውናል። ባለፈው ዓመት ሙክት ከ20 ሽህ ብር በላይ እንደነበር ያወሱት አቶ ሹመት በዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አካባቢ ያለው ሰላም ገበያው እንዲረጋጋ አግዟል ነው ያሉት።
የዳልጋ ከብት ዋጋ ከአምናው ዋጋ አንጻር የተሻለ ነው ያሉት ደግሞ አቶ ሞገስ አላዩ ናቸው። የደለበ በሬ ከ25 ሺህ እስከ 45 ሺህ ብር እየተገበያየን ነው ብለዋል። የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት የእንሰሳት እና እንሰሳት ተዋጾኦ ቡድን መሪ ደሴ ገበያው ዶሮ ከ200 እስከ 400፣ ፍየል ከ5 ሺህ እስከ 17 ሺህ፣ የዳልጋ ከብት ከ20 ሺህ እስከ 52 ሺህ ድረስ እየተሸጠ ነው ብለዋል።
የበዓል ገበያው ከአጎራባች ክልል የመጡ ነጋዴዎችም የተሳተፉበት እንደኾነ ያወሱት አቶ ደሴ ከአምናው የትንሳኤ በዓል ገበያ ጋር ሲነጻጸር የዘንድሮው የበዓል ገበያ ተመጣጠኝ ዋጋ የታየበት ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!