
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የጎንደር ከተማ ነዋሪው ወጣት መላኩ ታደሰ ከመንግሥት ሠራተኛነት ለቆ ወደ ዶሮ እርባታ ከገባ ዓመታት ተቆጥረዋል። አቶ መሰለ ገረመው ደግሞ በማድለብ ሥራ ተሰማርተዋል። የእንስሳት ተዋፅኦ ሥራ ቀላል፣ አትራፊ እና ቤተሰብን ለመምራት እንደሚያስችል ሁለቱም ገልጸዋል።
ዘንድሮ የገበያ ችግር እንደነበረባቸው ገልጸው እንዳይከስሩ ምርታቸውን ተሯርጠው እንደሚሸጡ ነው የገለጹት። የሥራ ቦታ፣ የገበያ ትስስር እና የብድር አቅርቦት ቢመቻች የበለጠ እንደሚሠሩም ተናግረዋል። በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት የእንስሳት ምርት ተዋጽኦ ባለሙያ መላኩ ደምሌ በከተማ አሥተዳደሩ በ36 የከተማ እና ገጠር ቀበሌዎች ለዘርፉ ልማት ትኩረት ተሠጥቶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በርካታ ግለሰቦች፣ ኢንተርፕራይዞች እና ማኅበራት በማድለብ ሥራ መሠማራታቸውንም ገልጸዋል።
በዚህም 16 ሺህ 300 የሚኾን በግ እና ፍየል፣ ከ10 ሺህ 400 በላይ ዶሮ፣ ከ14 ሚሊየን በላይ እንቁላል ለበዓል መዘጋጀቱን ጠቅሠዋል። የገበያ ቦታ ተመቻችቶ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ በከንቲባ ኮሚቴ እየተመራ መኾኑንም ተናግረዋል። የመሥሪያ እና የገበያ ቦታ እንዲኹም መሠረተ ልማት የማሟላት ሥራዎች እየተሠራ ቢኾንም የወጥነት ችግር መኖሩን አልሸሸጉም።
በአማራ ክልል የእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት የእንስሳት ሃብት ልማት ባለሙያ ደመላሽ አይችሌ ለትንሳኤ በዓል እንስሳትን እና ተዋጽኦዋቸውን የማምረት ሥራ በትኩረት መሠራቱን ገልጸዋል። ባለሙያው ጨምረውም የእንሥሣት ምርትን ለማሳደግ ለእንሥሣት መኖ ማቅረብ፣ የተሻሻሉ የእንሥሣት ዝርያዎችን ማዳቀል፣ ገበያ የማፈላለግ እና ሌሎች ጠቃሚ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል። በዚህም የተሻለ ምርት እንደተገኘ ገልጸዋል።
በተከሰተው የጸጥታ ችግር እንደልብ መንቀሳቀስ ባለመቻሉ የገበያ ውሥንነቶች ቢኖሩም ያሉትን አማራጮች ለመጠቀም ተሞክሯልም ነው ያሉት። የወተት ገበያ ትስስር መፍጠርን በምሳሌነት ያነሱት ባለሙያው ለባሕር ዳር የመንግሥት ሠራተኞች በየመሥሪያ ቤታቸው እንዲቀርብ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በሀገር ደረጃ በመሥሪያ ቦታ፣ በገበያ እና በብድር አቅርቦት በኩል የነበረውን ማነቆ ለመፍታት መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ በ”ሌማት ቱሩፋት” እየሠራ መኾኑን የገለጹት አቶ ደመላሽ አይችሌ ከባለድርሻ አካላት ጋር በተሻለ ትብብር እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል። በቅርቡ በስምንት ሜትሮፖሊታን ከተሞች ብቻ 63 ሸዶች መገንባታቸውንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!