
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አብዝታ የምትወደውን፤ በቅድስና፣ በድንግልና ያረገዘችውን፣ በቅድስና በድንግልና የወደለችውን፣ ልጄ ወዳጄ እያለች የምትጠራውን፣ በንጽሕት ከንፈሯ እየሳመች ያሳደገችውን፣ በቅዱሳን እጆቿ ያቀፈችውን፣ በተባረከች ጀርባዋ ያዘለችውን፣ ከጡቷ ወተት ያጠባችውን፣ ዓይታ የማትጠግበውን ልጇን ሰቅለውታልና አብዝታ አለቀሰች፡፡
ደም ግባቱ እጅግ ያማረውን፣ ጌታዋን የወለደች ናትና እንደ እናት ልጄ የምትለውን የተወደደ ልጇን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ አይተዋለችና ኃዘኗ እጅግ መረረ፡፡ ብዙ እናቶች አንደኛው ሲሞትባቸው በሌላኛው ይጽናናሉ፣ እርሷ ግን አንድ ነው ያላት፣ እርሱንም ሰቅለውባታል፤ በችንካር ቸንከረውባታል፣ ነፍሱንም በፈቃዱ አሳልፎ ሰጥቷልና የምትጽናናበት፣ ዓይኗን የምታሳርፍበት፣ ኃዘኗን የምትረሳበት ልጅ አልነበራትም፡፡ አያሌ መከራዎችን የተቀበለችበትን፣ አያሌ ፈተናዎችን ያለፈችበትን ልጇን ተሰቅሎ ባየችው ጊዜ አብዝታ አለቀሰች፣ አምርራ አዘነች፡፡
በመስቀሉ ግርጌ ኾና ወዮ አለች፤ ስለ ልጇ መከራ አዘነች፣ ስለ ልጇ መከራ ደረቷን ደቃች፡፡ ልጇ ወዳጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሏልና ቅድስት ድንግል ማርያም አንጀቷ ተላወሰ፡፡ አበው በድንግልና ስለ ጸነሰችው፣ በድንግልናም ስለ ወለደችው ስለ ተወደደ ልጇ ለምን አታላቅስ? የድንግልና ወተቷን እያጠባች ስላሳደገችው ልጇ ለምን አታለቅስ? በስደት ስለ ተንከራተተችበት ልጇ ለምን አታለቅስ? ይላሉ የእርሷን ኃዘን ባሰቡ ጊዜ፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በባሕር ዳር ሀገረ ስብክት የአራቱ ጉባኤያት መምህር ሊቀ ሊቃውንት ስመዓኮነ መልአክ እመቤታችን በአይሁድ ዘንድ የሚደረገውን ዝግጅት ታወቅ ነበር፡፡ ልጇ ተይዞ እንደሚሞትም አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ መያዙን በሰማች ጊዜ ከዮሐንስ ጋር በኃዘን ወደ ቀራንዮ ሄደች፡፡ በቀራንዮ በደረሰችም ጊዜ ርቃኑን ልጇን አይታዋለች፡፡ የቆሰለ ሰውነቱን ተመልክታዋለች፡፡ ተጠማሁ ሲልም ሰምታዋለች ይላሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ኃዘኗን አከበዱባት፡፡ ዋይታዋን አጠነከሩባት፡፡ የድንግልና ወትት ያጠባችው ልጇ ተጠማው ሲል ማስማት፣ እጅግ የተዋበው ደም ግባቱ በደም ተሸፍኖ ስታየው እንደምን አታዝን?
ቅዱሳን አንስት አልቀሰውለታል፤ መከራውን የተመለከቱትም አንብተውለታል፤ ማርያም መግደላዊት እጅግ ታለቅስ ነበር፡፡ የእርሷም ለቅሶ ከሌሎች የተለየ ምክንያት ነበረው፡፡ አጋንንትን አስወጥቶላታል፤ ጤንነቷን መልሶላታልና፡፡ እርሷ ወዳጅና ዘመድ በረሳት ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ ደርሶላት ነበርና፡፡ እርሷ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለ ጊዜ ሕይወቴ አንተ ነህ፣ መድኃኒቴም አንተ ነህ፣ ሌላ ሰው የለኝም፣ ዘመድ የለኝም፣ ለአንተ ይሄ አይገባህም እያለች ማርያም መግደላዊት ታለቅስ ነበር፡፡ የእናቱ የቅድስት ድንግል ማርያም ኃዘን ግን ከሁሉም የላቀ ኃያል እና የመረረ ነበር፡፡
ላሐ ማርያም ወሰቈቃወ ድንግል በተሰኘው መጽሐፍ ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ሀዘን እንዲህ ተጽፏል፡- ልጄ ኾይ እኔማ በልቤም እንግዲህ በዓላችንን እናከብር ዘንድ ፋሲካ ደርሷልና ወደሀገራችን እንመለሳን እያልኹ በእየለቱ ደስ ብሎኝ ነበር፡፡ ልጄ ወዳጄ ኾይ ነገር ግን ፋሲካዬ በለቅሶና በኃዘን ተለወጠ፡፡ በዓሌም ወደ ዋይታ ደስታዬም ወደ ልብ ሰባሪ ሀዘን ተመለሰ፡፡ ልጄ ወዳጄ ኾይ ስለ ልጇ የእናት ኃዘን የከበደ ነው፡፡ የወዳጅም ሀዘን በወዳጅ ሀዘን የጸና ነው፡፡ ወዳጄ ልጄ ኾይ ከኹላቸው ከእስራኤላውያን ኃዘን ይልቅ የኔ ኃዘን ይበልጣል፡፡
ልጇ በመስቀል ላይ የዋለባት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቀራንዮ በሔደች ጊዜ እየፈጠነች ስትገሠግሥ የሚያዩዋት ሰዎች ሁሉ እርስ በእርሳቸው እንደዚህ እየጮኸች የምታለቅስ ይህች ማን ናት ይባባሉ ነበር፡፡ ሌሎችም “ይህቺንስ የምትሻውን ከዚህ ገበያ ስትገዛ አይተናት አናውቅም” አሉ፡፡ ሌሎቹም እርስ በእርሳቸው ይህቺ አዲስ የመጣች ናት በደንጋጤ በአደባባይ ትዞራለችና አሏት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንደኾነ የሚያውቁ ይህቺ እንደዚህ የምትፋጠን ልጇን በመስቀል እንደተሰቀለ ልታይ ይኾንን እንጃ ተባባሉ፡፡ ሌሎችም ስለ ልጇ ነግረዋት ይኾናል አሉ፡፡ ሌሎችም ደም ግባቷ የፊቷ ሞገስ ምንኛ ደስ እንደሚያሰኝ ተመልከቱ ተባባሉ፡፡ ሌሎችም እንደዚህች ያለች በዚህች ከተማ ውስጥ አላየንም፡፡ መልኳም የልጇን መልክ ይመስላል አሉ፡፡
አንተም ልጄ ኾይ በራስህ ላይ ያደረጉት የእሾህ አክሊል በራሴ ላይ ተደርጎ በአንተ ፈንታ መከራ መከራውን ኹሉ በትዕግሥት እቀበል ዘንድ በወደድሁ አለች ተብሎ ተጽፏል፡፡ ኃዘኗም እጅግ የመረረ ነበር፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል አጠገብ እናቱ፣ ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን አንቺ ሴት እነሆ ልጅሽ አላት፡፡ ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን እናትህ እነኋት አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት እንዳለ መጽሐፍ የእናቱን ኃዘን ያየው ልጇ እነኋት እናትህ ሲል ለዮሐንስ ሰጠው፡፡ ከሰማይና ከምድር የበለጠች እናት የተሰጠው ዮሐንስ ምንኛ የታደለ ነው? አምላክን የወለደች እናት የተሰጠው ዮሐንስ ምንኛ የተመረጠ ነው? አምላክን ልጄ ብላ የምትጠራውን እናት እነኋት የተባለው ዮሐንስ ምንኛ የታደለ ነው?
አባ ሕርያቆስ የድንግል ማርያምን ኃዘን ከያዕቆብ ኃዘን ጋር ያነጻጽረዋል ይላሉ ሊቁ፡፡ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ ያዘነው ኃዘን ከሚያስገርሙ ኃዘናት መካከል አንደኛው ነው፡፡ የድንግል ማርያም ኃዘን ግን ከዚህ ይልቃል፡፡ ስለ ምን ቢሉ ያዕቆብ ልጁ መሞቱን ሰማ እንጂ የሞተውን ልጁን አላየውም፡፡ ድንግል ማርያም ግን የልጇን መሞት ብቻ አልሰማችም ልጇን ፊት ለፊት ቆማ አይታዋለች፡፡ ያዕቆብ ልጁን አውሬ በላው አሉት እንጂ የተበጣጠሰ ሰውነቱን አላሳዩትም፡፡
ድንግል ማርያም ግን የተገረፈ ሰውነቱን፣ የተወጋ ጎኑን አይታዋለች፡፡ ያዕቆብ የልጁን ልብሱን ትተውለታል ማዕዛውን እያሸተተ፣ ልብሱን እያወዘዋዘ ያለቅስ ነበር፡፡ ድንግል ማርያም ግን ልብሱን እንዳታለቅስበት አይሁድ ተካፍለው ወስደውታል፡፡ ያዕቆብ የሚጽናናባቸው ልጆች ነበሩት፤ ድንግል ማርያም ግን የምትጽናናበት ሌላ ልጅ የላትም፡፡ አንድ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር እርሱም በመስቀል ላይ ተሰቅሏል፡፡ በምንስ ትጽናናለች? ያዕቆብ የሚያጽናኑት ነበሩ ድንግል ማርያም ግን የሚያጽናናት ወዳጅም ዘመድም አልነበራትም፡፡ እናትና አባቷም አስቀድመው አርፈዋል፡፡ ጠባቂዋ አረጋዊ ዮሴፍም መጥቶ እንዳያጽናናት እርሱም ሞቷል፡፡ ከያዕቆብም ኃዘን የድንግል ማርያም ኃዘን ይበልጣል፡፡
ሊቁ እንደሚሉት የድንግል ማርያም ኃዘን በአንደበት የሚናገሩት፣ በቃላት የሚገልጹት አይደለም፤ በከበድ ኃዘን ላይ ወድቃለችና፡፡ ትንሣኤውን ደግሞ ከእናቱ አስቀድሞ ለሌሎች አንስት ነገራቸው፡፡ ስለ ምን ቢሉ ትንሣኤ የሚያስፈልጋቸው ለሀጢአተኞች ነውና፡፡ ለእናቱማ ቢነግራት ምኑ ይገርማል፤ እርሱ ግን ለሀጢአተኞች ነገራቸው ነው የሚሉት፡፡
እናት መድኃኒት ናት፣ እናት ምክንያተ ሕይወት ናት፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመስቀሉ ግርጌ እነኋት እናትህ ብሎ ለዮሐንስ እንደሰጣት ሁሉ ማርያምም በዚያን ጊዜ በዮሐንስ አማካኝነት ለእኛም ሰጠን ይላሉ፡፡ በዚህም ሁልጊዜ እናታችን እንላታለን፤ ሲጨንቀንም ድረሽልን፣ አማልጅን እንላለን፡፡ ሀጢአትም ስንሠራ ሰዓሊለነ ቅድስት እያልን እንጸልያለን ነው የሚሉት፡፡ ማርያም በዚች ቀን አብዝታ አዝናለች፤ በተቀደሱ ዓይኞቿ እንባን አፍስሳለች፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!