
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ክርስቶስ ንጹህ አምላክ ሳለ፣ ሰማያዊ አምላክ ኾኖ ሳለ፣ እንደ በደለኛ በአይሁድ እጅ ተገረፈ፤ ተገርፎም አልቀረ በቀራንዮ አደባባይ በመስቀል ላይ ተሰቀለ። አይሁድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ጠልተውታል እና ማስወገድ ፈለጉ። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳም በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ በመስቀል ላይ ዋለ። መስቀሉ ሰባት እፅዋት ተሠብሥበው በሙሻ ዘር ተያያይዘው የተሠራ ነበር ይላሉ በጽርሐአርያም ደብረ ሲና በዓታ ለማርያም አንድነት ገዳም የስብከተ ወንጌል ክፍል ኀላፊ መምህር አብርሃም ሞላ፡፡
መስቀሉ እርጥብ ነበርና እጅግ ይከብዳል። ይህን እርጥብ መስቀል ጌታችንን አሸክመው ከጲላጦስ አደባባይ እስከ ቀራንዮ እየገፉ፣ እያዳፉ ወሰዱት። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ተሸክሞ ተራራ ሲወጣ ያዘነለት፣ የራራለት ሰው አልነበረም። እሱ ግን የሰው ልጅን ሲፈጥረው ከመላዕክት አልቆ ነበር የፈጠረው። የሚያይበት ዐይን፤ የሚያስብበት ጭንቅላት ፈጥሮለት ሳለ ማስተዋል ተሳነው። ከሁሉም አልቆ ፈጥሮት ሳለ፤ ከሁሉም ያነሰ ኾነ ይላሉ መምህሩ።
ስድስት ሰዓት አዳም እና ሔዋን አትብሉ የተባሉትን እፀ በለስ በልተው ከገነት የተባረሩበት ሰዓት ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገነት በተባረሩበት ሰዓት ወደ ቀደመ ርስታቸው ሊመልሳቸው በስድስት ሰዓት በመስቀል ላይ ተሰቀለ። ስድስት ሰዓት ፀሐይ ይበዛል። ፀሐይ ሲበዛ አዕምሮ ይበተናል። አዕምሮ ሲበተን ሰይጣን ይበረታል። ጌታም በዚህ ሰዓት ተሰቀለ።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስድስት ሰዓት ሲሰቀል በሰማይ ሦስት፤ በምድር አራት ታምራት ተደርገዋል። በሰማይ ፀሐይ ጨለመች፣ ጨረቃ ደም ለበሰች፣ ከዋከብት ረገፉ፣ በምድር መቃብራት ተከፍተው ከ500 የሚበልጡ ከ600 የሚያንሱ ሙታን ተነስተዋል። ድንጋዩ ተሰነጣጥቋል፣ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ለሁለት ተሰንጥቋል፣ ጨረቃ ደም ለበሰች ስንል ደም መልበስ ሳይኾን የፈጠረንን አምላክ እርቃኑን አናሳይም ሲሉ ሁሉም ብርሃናቸውን ከለከሉ ለማለት ነው ይላሉ መምህር አብርሃም። አይሁድ ግን የፈጠራቸውን አምላክ ራቁቱን በመስቀል ላይ አውለውታል።
ከስድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት 13 ሕማማተ መስቀል አድርሰውበታል ወይም መከራዎችን አድርሰውበታል። የመጀመሪያው አክሊለ ሶክ ነው። እሾህ ታትተው በራሱ ላይ ደፉበት “የአይሁድ ንጉስ አንተ ነህ፣ ዘውድ ይገባሃል” እያሉ ይሳለቁበት ነበር። ራስ ራሱን በዘንግ መቱት፣ ፊቱን በጨርቅ ሸፍነው በጥፊ ይመቱት ነበር። ንጉስ ነኝ ትላለህ ማን ነው የመታህ እወቅ እስኪ ይሉት ነበር። ምራቃቸውን ይተፉበት ነበር። ተጠማሁ ባለ ጊዜ ሀሞት እና ከርቤ ቀላቅለው አጠጥተውታል።
የሰጡት ሀሞት አንጀት በጣጥሶ የሚጥል ቢኾንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ምንም አልኾነም ነበር። ተጠማሁ ያለ “ፍቅር” ነው። እርሱን ፍቅር ስቦት ከሰማ ሰማያት ወረዶ፣ ከድንግል ማርያም ተወልዶ፣ በ30 ዓመቱ ተጠምቆ በጌቴሴማኒ ያለምግብ እና ውኃ 40 ቀን እና 40 ሌሊት የጾመው አምላክ ከተያዘ ጀምሮ 18 ሰዓት ሳይሞላው ተጠማሁ ያለ “ፍቅር” ነበር ይላሉ መምህር አብርሃም።
አይሁድ ጠልተውታልና ከልጅ እስከ አዋቂ ፈርደውበታል እና ከማኅበራዊ ኑሮ እንገለላለን፣ መከራ ያደርሱብናል ሲሉ አብረው ይተባበሩ ስለነበር ፍቅር ጠማኝ አለ። ጀርባውን ገርፈውታል፣ ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ አዴራ እና ሮዳስ በተባሉ ችንካሮች በመሥቀል ላይ ቸነከሩት እነዚህ 12 ሲኾኑ 13ኛው ቅድስት ነፍሱ ከቅዱስ ሥጋው ከተለየ በኋላ ለንጊኖስ ጎኑን በጦር የወጋው ነው ብለዋል መምህሩ፡፡
በቀራንዮ አደባባይ በእፀ መስቀል ላይ የተሰቀለው አምላክ ፍቅር ስቦት ፍቅር አገብሮት ነው ወደዚች ምድር የመጣ ይላሉ መምህር አብርሃም፡፡ አዳም እና ሄዋን ወደ በለሷ በመሄዳቸው እግሩ ተቸነከረ፣ በእጃቸው በመቁረጣቸው እጁ ተቸነከረ ብለዋል፡፡ አዳም እና ሄዋን እፀ በለስን በበሉበት ሰዓት ከበደል ያድናቸው፤ ዳግም ልጅነት ይሰጣቸው ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቀለ፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!