የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ መኾኑን የአማራ ክልል የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለሥልጣን ገለጸ።

14

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለትንሣኤ በዓል የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ መኾኑን የአማራ ክልል የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለሥልጣን ገልጿል። የአማራ ክልል የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለሥልጣን ምክትል ኀላፊ የዝና ደስታ በክልሉ በ12 ዞኖች እና በስምንት ከተማ አሥተዳደሮች የገበያ ማረጋጋት ሥራ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል፡፡

በዚህ ሳምንት ብቻ በማዕከላዊ ጎንደር፣ በደቡብ ወሎ፣ በሰሜን ወሎ፣ በምዕራብ ጎጃም ዞኖች፣ በደሴ፣ ጎንደር፣ ባሕር ዳር፣ ኮምቦልቻ፣ ደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደሮች እና ኦሮሞ ብሔረሰብ እና ዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደሮች የተለያዩ ምርቶችን በማቅረብ ገበያ የማረጋጋት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት።

በዚህም ከ190 ሺህ ኩንታል በላይ የተለያዩ ሰብሎች፣ የባልትና ውጤቶች፣ የዳቦ ዱቄት፣ ስኳር፣ ማካሮኒ፣ ቅቤ ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል። ከዚህም ባለፈ እንቁላል እና አይቭ የማቅረብ ሥራ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል። ከአራት ሚሊዮን 181 ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት እና ወተት ማቅረብ መቻሉን ጠቅሰዋል። በዚህም ገበያ የማረጋጋት ሥራ 1 ሺህ 221 የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት እና 114 ሁለገብ ኅብረት ሥራ ማኅበረት ገበያ የማረጋጋት ሥራ ላይ መሳተፋቸውን አስታውቀዋል።

ከዚህም ባለፈ በወልድያ ከተማ አሥተዳዳር ለሚገኙ 587 የመንግሥት ሠራተኞች በሦስት ወራት የሚመለስ ከ2 ሚሊዮን 900 ሺህ ብር በላይ ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል። ለ122 ኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ ወረዳ እና ከተማ አሥተዳደሮች ለገበያ ማረጋጊያ የሚውል ተጨማሪ ከ320 ሚሊዮን ብር በላይ መለቀቁን አንስተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“እየተከናወነ ያለው መተሳሰብ እና መደጋገፍ አንድነትን ያጠናክራል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleክርስቶስ ለምን በስድስት ሰዓት ተሰቀለ?