
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሕይዎት መብል የኾነችው፣ ለዘላለም የማታስርበው፣ የተቀደሰችው ሥጋ ተወጋች፣ በግፍ ተቆረሰች፣ የሕይወት መጠጥ የኾነችው፣ ለዘለዓምም የማታስጠማው የተቀደሰችው ደም ፈሰሰች፤ ድውያነ ነፍስን የምታነጻው፣ ከማር እና ከወተት የምትጣፍጠው አንደበት መራራ ሐሞትን ተጎነጨች፣ ዓለማትን አስውባ የሠራች እጅ ተቸነከረች፤ በአርያም የምትረማመደው እግር በሚስማር ተመታች፡፡
መላዕክት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ የሚያመሰግኑትን፣ ያለ ማቋረጥ የሚሰግዱለትን፣ እየተፋጠኑ የሚታዘዙለትን፣ ነብያት የተነበዩለትን፣ አዳምና ልጆቹ በተስፋ የጠበቁትን፣ የሲኦል ነፍሳት ጌታ ሆይ ናልን ያሉትን ገፉት፣ አዳፉት፣ አብዝተው ገረፉት፣ በጦር ወጉት፣ መስቀል አሸክመው ከምዕራፍ ምዕራፍ አሰቃዩት፣ መግረፉም፣ መዳፋቱም፣ መውጋቱም፣ መራራ ሐሞት ማጠጣቱት፣ መዘባበቱም አልበቃቸው ሲል ቸንክረው በመስቀል ላይ ሰቀሉት፡፡
ጌታዋ የተሰቀለባት ምድር ተናወጸች፣ ተጨነቀች፣ ተጠበበች፣ አምላኳ የተሰቃየባት ሰማይ ደነገጠች፣ ምድርን ጨለማ ጋረዳት፣ ሰማይንም ጨለማ ከበባት፡፡ ከሀዲዎች አሳልፈው ሰጡት፣ ሀሰተኞች ከሰሱት፣ በሀሰተኞች ፊት አቆሙት፣ ሀሰተኞች ፈረዱበት፣ ሀሰተኞችም ሰቀሉት፡፡ አመጸኞች እውነት የኾነውን ክርስቶስን ስቀልልን፣ በርባንን ፍታልን እያሉ ደነፉ፡፡ ገዥዎችም እንዳሉት አደረጉላቸው፡፡
ፍጡራን ፈጣሪያቸውን ወገሩት፤ አሰቃዩት፤ እውነተኛውን እንደበደለኛ ቆጠሩት፤ ክፉ እንዳደረገ መከራን አበዙበት፤ ሁሉን ማድረግ የሚቻለው፣ በሁሉም የሚገኘው፣ ሁሉንም የሚያውቀው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ፍቅር ራሱን አሳልፎ ሰጠ፡፡ እስከ ሞት ድረስ ማፍቀር እንደምን ያለ ፍቅር ነው? ተበድሎ ለመካስ መምጣት እንደምን ያለ ቸርነት እና ደግነት ነው? ጥፉ ብሎ ማጥፋት ሲችል ዝም ማለት እንደምን ያለ ዝምታ ነው? የሚያሰቃዩትን ከምድረ ገጽ ማጥፋት ሲቻለው መታገስስ እንደምን ያለ ትዕግሥት ነው? እጹብ ከማለት ውጭስ ምን ይባላል?
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በባሕር ዳር ሀገረ ስብክት የአራቱ ጉባኤያት መምህር ሊቀ ሊቃውንት ስመዓኮነ መልአክ ስቅለት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መከራ የሚታሰብበት፣ ለሰው ልጅ ማዳን ሲል በቀራንዮ ራሱን አሳልፎ የሰጠበት እና የተሰቀለበትን የምናስታውስበት፣ የምናከብርበት በዓል ነው ይላሉ፡፡
ስቅለት የ5 ሺህ 500 ዘመናት የሰው ልጅ ካሳ የተከፈለበት፣ ማድነቅ ካልኾነ በስተቀር ተነግሮ የማያልቅ ፍቅር፣ ቸርነት የተፈጸመበት፤ አምላክ የሰውን ልጅ ፍጹም የወደደበት ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሲል ሞቷል፤ ያለ ሀጢያቱ ሞቷል፤ ከሳሾቹም፣ ፈራጆቹም ወንጀል ያላገኙበት፣ ወንጀልም ያልተገኘበት ኾኖ ሳለ መሞቱ ያስገርማል፤ ወንጀል ሳይገኝበት ስለ ሀጢያተኖች መሞቱ ደግሞ እጅግ ያስደንቃል ነው የሚሉት፡፡
ከተማውን ያስመረረ፣ ሕዝቡን ያስቸገረ በርባን የሚባልን ወንበዴ ልቀቅልን፣ ኢየሱስን ግን ስቀልልን አሉት፤ የተደረገበት ሁሉ በፈቃዱ ነውና ያስደንቃል፤ መያዙን፣ መሰቃየቱን፣ መሰቀሉን መሞቱን አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ ኢየሱስም የሚመጣበትን ሁሉ አውቆ ወጣና ማንን ትፈልጋላችሁ አላቸው። የናዝሬቱን ኢየሱስ ብለው መለሱለት። ኢየሱስ እኔ ነኝ አላቸው። አሳልፎ የሰጠውም ይሁዳ ደግሞ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር። እንግዲህ እኔ ነኝ ባላቸው ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍገው በምድር ወደቁ። ደግሞም ማንን ትፈልጋላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም የናዝሬቱን ኢየሱስን አሉት። ኢየሱስ መልሶ እኔ ነኝ አልኋችሁ፤ እንግዲህ “እኔን ትፈልጉ እንደ ኾናችሁ እነዚህ ይሂዱ ተውአቸው” አለ እንደተባለ ይህም ቃል በኃይላችን ያዝነው እንዳይሉ ምስክር የኾነ ነው፤ ወድቀው የነበሩት ተነስተው የያዙት በፈቃዱ እንጂ በኃይላቸው አይደለምና ይላሉ፡፡
ሊቀ ሊቃውንት እንደሚሉት እርሱ ለመሞት ነው የመጣው፣ ማንም ቢኾን ወደ ዓለም ሲመጣ በፈቃዱ ሊመጣ አይቻለውም፤ ለመሞትም ወስኖ አይመጣም፤ የሚሞት ሥጋ ተሸክሞ ስለሚመጣ ይሞታል እንጂ፤ እርሱ ግን በፈቃዱ መጣ፣ ለመሞትም መጣ፤ እስከ ስቅለቱ ቀንም የቆየው ሕግን መፈጸም ስለነበረበት ነው፡፡
በስቅለቱ ስለተቀበለው መከራ ሲናገሩ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ያዙት፣ አሠሩት፣ በዳኛ ፊት አቆሙት፣ ምራቅ ተፉበት፣ መራራ ሀሞት አጠጡት፣ መስቀል አሸክመው እጁን ወደኋላ አስረው መሬት ላይ ገፉት፣ ጣሉት፤ ከላይ ያለው ቀጠቀጠው፣ ከታች ያለው መታው በዚህም ጊዜ ፍጥረታት ሁሉ ደነገጡ፤ ስለ ምን ቢሊ የወደቀው የሰማይ እና የምድር አምላክ ነውና፤ በጫፉ ላይ የሚጠዘጥዝ ሦስት ሦስት ልሳን ባለው ጅራፍ ገረፉት፣ ፊቱን በጥፊ መቱት፣ ፊቱን በጥፊ በሚመቱበት ጊዜም ፀሐይ ጨለመች፣ ጨረቃም ደም ለበሰች፣ ስለ ምን ቢሉ ዓለም ብርሃን የምትኾነው ከፊቱ ብርሃን የተነሳ ነውና፤ በቀኖት ቸነከሩት፣ በጦር ወጉት፣ የሾህ አክሊል ደፉበት፣ የሾህ አክሊሉም ራሱን ዘልቆ ይገባ ነበር፤ በመስቀል ላይ ሰቀሉት ነው ያሉት፡፡
በዓለም ላይ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኾኖ በጅራፍ የተገረፈ የለም፤ ግርፋቱ አጥንቱ እስኪታይ ነበርና ቁጥሩም የበዛ ነው ይላሉ መምህሩ፡፡ ጌታ ኢየሱስ በተሰቀለ ጊዜ ሰባት ታምራት ታይተዋል፤ ሦስቱ በሰማይ፣ አራቱም በምድር፡፡ በሰማይ ፀሐይ ጨለመች፣ ጨረቃ ደም ለበሰች፣ ከዋክብትም ብርሃናቸውን ነሱ፤ ከስድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት በምድር ላይ ምንም ዓይነት ብርሃን አልነበረም፤ እነዚህ ሦስት ሰዓታት ጌታ ከነነብሱ በመስቀል ላይ የነበረባቸው ሰዓታት ናቸው፤ ጌታ በመስቀል ላይ ለአምስት ሰዓታት ቆይቷል፡፡
በምድርም አራት ታምራት ተደርገዋል፤ መቃብራት ተከፍተዋል፤ ሙታን ተነስተዋል፤ ዓለቶች ተሰነጣጥቀዋል፤ የቤተ መቅደስ መጋረጃዎች ተከፍለዋል፤ የመጋረጃ መከፈትም እግዚአብሔር የአይሁድን ቤተ መቅደስ እንዳሳለፈው ለማሳየት ነው፣ የሐዲስ ኪዳኑ መቅደስ ራሱ ኢየሱስ ክርስቶሰ ነው፣ የሐዲስ ኪዳን መስዋዕትም ራሱ ክርስቶስ ነው፣ መቅደሳቸውን አሳለፍኩት ሲል መጋረጃውን ቀደደ፤ የሙታንም መነሳት ክርስቶስ የሞተው ለሰው ልጆች ድኅነት ነውና ለዚያ መልክት ነው፣ የመቃብሩም መከፈት የሲኦል መከፈት ምልክት ነው፣ ከዚህ በኋላ የሰው ልጅ በመቃብር አይኖርም የሚለውን ያጠይቃል፤ በስቅለቱ የታዩት ታምራት ነገረ ድኅነትን የያዙ ምስጢራት ናቸው ይሏቸዋል ሊቀ ሊቃውንት፡፡
ሊቀ ሊቃውንት እንደሚሉት ክርስቲያን የክርስቶስን ማሕትም ተሸክሞ የሚኖር ነው፤ ክርስቶስ በምድር ላይ ቢፈለግ መገኘት ያለበት በክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ ነው፤ ሐዋርያት ክርስቶስን መስለው ኖረዋል፤ የክርስቲያን መለኪያው ክርስቶስን መምሰል ነው፤ ትልቁ ሰማዕትነት በፍቅር መኖር ነው፤ ሰውን መውደድ ትልቅ መስዋዕትነት ነው፤ አንድ ሰው ለሰዎች ፍቅርን መስጠት ከቻለ ታላቅ ነገርን አድርጓል፤ ክርስቶስ በምድር ላይ ምንም ነገር አልነበረውም፤ ሃብት እና ንብረት፣ ቤትም የለውም፤ እኛም የተከተልነው ፍቅሩ ስቦን ነው፣ ክርስቶስም ለዓለም የሰጠው ፍቅሩን ነው፣ ፍቅር ማለት ራስን መስጠት ነው፤ ክርስቶስን አገለግላለሁ ያለ ከሰዎች ጋር በፍቅር መኖር አለበት፡፡
በምድር ላይ ቢገድሉን መገደል የክርሰቶስ መንገድ ነው፣ ብንገድል ግን የክርስቶስ መንገድ አይደለም፤ ክርስቶስ ሳይገድል የተገደለ፣ ሳይበድል የተበደለ ነውና፤ ሳንበድል ብንበደል፣ ሳንገድል ብንገደል ክርስቶሳዊነት ነው፣ ትልቁ መንፈሳዊነት ነው፤ ትልቁ ሕይወትም ፍቅር ነው፡፡ ክርስትናችን ሕያው የሚኾነው ፍቅር ሲኖረን ብቻ ነው፣ ስትጸልዩም በፍቅር፣ ስትጾሙም በፍቅር፣ መስዋዕት ስታስገቡም በፍቅር ይሁን፣ ሁሉም ቦታ ፍቅርን የምናስገባው ክርስቶስ የሰጠን ትልቁ ስጦታ ስለኾነ ነው ይላሉ፡፡
የሰው ልጅ ትዕዛዙ በፍቅር መኖር ነውም ብለዋል መምህሩ፡፡ የክርስቶስ መከራ ለሰው ልጆች የተከፈለ መከራ ነው፤ በምንም የማይገኘው ስጦታ የክርስቶስ ራስን መስጠት ነው፤ እግዚአብሔር የወደደውን ሰው እንውደድ፣ የእርሱን ሕማም እያሰብን ሌሎችን ሰዎች ብናሳምም ክርስቶስን ከወጉት፣ ካሰቃዩት ከአይሁድ ጎን መሰለፍ ነው ይላሉ፡፡
ራሳችሁን ለፍቅር አሳልፋችሁ ስጡ፡፡ ከራሳችሁም በላይ ሌሎችን ውደዱ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከራስ በላይ መውደድን፣ ለፍቅር ራስን አሳልፎ መስጠትን፣ ተበድሎ መካስን፣ ተበድሎ ይቅር ማለትን፣ ደግነት ማድረግን መከራው አሳይቷልና ነው ያሉት የኔታ፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!