“ለችግረኞች የምትሰጥ ትንሽ ድጋፍ የእነሱን ብዙ ጎደሎ ትሞላለች” የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር

12

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሁሉም ቤት ውስጥ በዓል አለ፤ ሁሉም ቤት ውስጥ ደስታ አለ፡፡ ይህ የሚኾነው ደግሞ ያለው ከሌለው ጋር ተካፍሎ በዓሉን ማክበር ሲችል ነው፡፡ በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለአቅመ ደካሞች እና ዝቅተኛ የገቢ ምንጭ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የበዓል መዋያ ድጋፍ ተደርጓል፡፡

ለችግር ተጋላጭ ለኾኑት የኅብረተሰብ ክፍሎች የዶሮ፣ የዳቦ ዱቄት፣ የአልባሳት፣ የጥሬ ገንዘብ፣ የእንቁላል፣ የዘይት እና መሰል የበዓል መዋያ ቁሳቁስ ነው ድጋፍ የተደረገው፡፡ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ሆፕ ፎር ጠባሴ በተባለ በጎ አድራጎት ማኅበር አማካኝነት ድጋፍ አድርገዋል፤ የከተማ አሥተዳደሩም በተዋረድ ተቋማት አማካኝነት ባለሃብቶችን፣ ኢንዱስትሪዎችን እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማሥተባበር ለችግር ተጋላጭ የኾኑ የከተማዋ ነዋሪዎች በችግራቸው ምክንያት በዓልን ተከፍተው እንዳይውሉ ድጋፍ አድርጓል፡፡

የደብረ ብርሃን ከተማ ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ በለጥሽ ግርማ እንደገለጹት በዚህ መልኩ ለ3 ሺህ 40 የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ድጋፍም በአጠቃላይ ከ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡ የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በድጋፍ አሰጣጥ

መርሐ ግብሩ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከመደጋገፍ ውጪ አማራጭ የለም ብለዋል፡፡ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው “ለችግረኞች የምትሰጥ ትንሽ ድጋፍ የእነሱን ብዙ ክፍተት ትሞላለች” ብለዋል፡፡ የከተማ አሥተዳደሩ በድሀ ተኮር መርሐ ግብሮች ጊዜያዊ እና ዘላቂ ድጋፍ እያደረገ መኾኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ ተግባሩ በመንግሥት አቅም ብቻ ውጤታማ ስለማይኾን አቅሙ የቻለ ሰው ሁሉ ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ድጋፍ የተደረገላቸው የከተማዋ ነዋሪዎችም ችግራቸው በመጠኑም ቢኾን ስለመቃለሉ ተናግረዋል። ለተደረገላቸው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ይሁን እንጂ ችግራቸው ከዚህ የከፋ ነውና ድጋፉ ከበዓላት ሰሞን የዘለለ ሊኾን እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቤቶችን ገንብቶ አስረከበ።
Next article“ምድር ተናወጸች፤ ሰማይም ደነገጠች”