
ደብረ ብርሃን: ሚያዝያ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የተገነቡት ቤቶች ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የተሠሩ ሲሆን በጠባሴ ክፍለ ከተማ ብቻ 31 ቤቶች ተገንብተው ተላልፈዋል ተብሏል፡፡ በሌሎች ክፍለ ከተሞችም ተጠናቅቀው ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የሚደርሱ ቤቶች መኖራቸው ተገልጿል።
አሁን ላይ ተገንብተው የተላለፉት ቤቶችን የተረከቡት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ የሚገኙ ወገኖች ቤት ማግኘታቸው ለቀጣይ የተሻለ ኑሮ ለመኖር እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል። በአሁኑ ሰዓት በከተማው 98 ቤቶች በመጠናቀቅ ላይ መኾናቸውን ከተማ አሥተዳደሩ አስታውቋል፡፡ በበጀት ዓመቱ 10 ሚሊየን ብር በመመደብ በከተማው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የቤት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት።
በግንባታ ላይ ያሉ ቤቶችን ለማጠናቀቅ እና በሁሉም ክፍለ ከተሞች ተደራሽ ለማድረግ የተጠናከረ ሥራ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል፡፡ አሁን ላይ የተገነቡትን ጨምሮ በቀጣይ የሚገነቡ ቤቶችን ፍትኃዊ በኾነ መንገድ ለተጠቃሚዎች የማስተላለፍ ሥራው በጥንቃቄ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ስንታየሁ ሀይሉ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!