
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)አዕምሯችን ከጠቅላላው የሰውነት ክፍል ሁለት በመቶ እንደሚመዝን ይነገራል። ይህም በሰውነት ውስጥ ካለው ጠቅላላ የደም አቅርቦት ከ15 እስከ 20 በመቶ የሚኾነውን እንደሚወስድ መረጃዎች ያሳያሉ። በዚህ የደም ዝውውር አማካይነት አዕምሮ ኦክስጅንን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን ያገኛል። ይህ የደም ሥር በተለያዩ ምክንያቶች ሙሉ በሙሉ ሲዘጋ እና በጭንቅላት ውስጥ የደም መፍሰስ አደጋ ሲያጋጥም ስትሮክ እንደሚከሰት የጤና ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ደም መፍሰስ ደግሞ የከፋው የስትሮክ ዓይነት እንደኾነ ያስቀምጣሉ።
የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው መረጃ ስትሮክ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ሁለተኛው ገዳይ በሽታ አድርጎ አስቀምጦታል። በየዓመቱ በዓለም 15 ሚሊዮን ሰዎች በስትሮክ እንደሚያዙም ይፋ አድርጎ ነበር። በስትሮክ ከሚያዙት ውስጥ አምስት ሚሊዮን ሰዎች እንደሚሞቱ፣ አምስት ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ለአካል ጉዳት እንደሚዳረጉም አመላክቷል። በሀገራችንም ተላላፊ ካልኾኑ 10 በሽታዎች አንዱ መኾኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ እና የማኅበረሰብ ጤና ስፔሻሊስት ሸጋው ማሩ (ዶ.ር) ከዚህ በፊት ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት በሽታው በሆስፒታሉ በውስጥ ደዌ ሕክምና ከፍተኛውን ቁጥር እየያዘ የመጣ እና ከፍተኛ የሞት መጠንንም እያስመዘገበ ይገኛል። በአብዛኛው ከዕድሜ መጨመር ጋር በተለይም ደግሞ ከ60 ዓመት በላይ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ይበልጥ እንደሚያጠቃም ነው የጠቀሱት።
ችግሩ በብዛት እድሜያቸው ከፍ ባሉ ሰዎች ላይ ቢከሰትም የደም ግፊት፣ የስኳር በሽታ፣ ኮሌስትሮል፣ የልብ ምት መዛባት፣ የደም ሥር መቁሰል፣ የሰውነት እንቅስቃሴ ችግር፣ ከፍተኛ ውፍረት፣ ሲጋራ ማጨስ እና አደንዛዥ እፅ በሚጠቀሙ በማንኛውም እድሜ ክልል በሚገኙ ሰዎች ላይም እንደሚከሰት አንስተዋል።
ጮማ እና ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች ማዘውተርም በደም ሥር ውስጥ ስብ እንዲከማች እና የደም ሥሮች እንዲዘጉ ወይም እንዲጠቡ በማድረግ ለስትሮክ እንደሚያጋልጥ ባለሙያው ገልጸዋል። በሽታው በተከሰተበት ወቅት ድንገተኛ የፊት መቀያየር፣ ልሳን መቆለፍ፣ ራስ ምታት፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ፣ ድንገተኛ የአካል አለመታዘዝ እና መፍዘዝ የመሳሰሉ ምልክቶችን ያሳያል።
ስትሮክ ቀድሞ ክትትል ከተደረገ ደግሞ መከላከል የሚቻል በሽታ እንደኾነም ገልጸዋል።
መፍትሔው ምን ይኾን?
👉 አመጋገብን ማስተካከል፣
👉ከመጠጥ፣ ከአደንዛዥ እፅ ወዘተ መራቅ ያስፈልጋል።
👉ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማዘውተር ይገባል።
የስትሮክ ምልክት እንደታየ በተቻለ ፍጥነት ወደ ሕክምና ተቋም ማምራት ያስፈልጋል። ጉዳቱ በደረሰ እስከ አራት ሰዓት ባለው ጊዜ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ጉዳቱን መቀነስ እንደሚቻል ገልጸዋል። ችግሩ ካጋጠመ በኋላ ደግም አስፈላጊውን የሕክምና ክትትል ማድረግ እንደሚገባ መክረዋል። ስትሮክ ካጋጠመ በኋላ ጉዳቶችን ለመቀነስ ‘ፊዚዮቴራፒ’ አስፈላጊ መኾኑን አብራርተዋል፡፡
መድኃኒቶችን መውሰድ፣ የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል፣ ስኳር፣ ግፊት እና ከልብ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ማስተካከል በሽታው እንዳይባባስ ያደርጋል ነው ያሉት። በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የድንገተኛ እና ጽኑ ሕሙማን ስፔሻሊስት ሐኪም ዶክተር ንጋት እንዳላማው ስትሮክ ቀደም ሲል “ያደጉ ሀገራት በሽታ” እየተባለ ይጠራ እንደነበር ገልጸዋል። አሁን ላይ በኢትዮጵያ የአኗኗር ዘይቤ እየተለወጠ በመምጣቱ በደም መጓጎል እና በደም መፍሰስ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መኾኑን አንስተዋል።
በተለይም ደግሞ በከተሞች አካባቢ በአመጋጋብ ምክንያት የኮሌስትሮል መጨመር፣ በገጠር አካባቢ ደግሞ የደም ግፊትን ቀድሞ ባለማወቅ ምክንያት የስትሮክ ተጠቂዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል ብለዋል። ሆስፒታሉ በተለያዩ አጋጣሚዎች ላይ በክልሉ ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎች እና መድኃኒት ቤቶች ምርመራ በሚያደርጉበት ጊዜ ለስትሮክ የሚያጋልጡ የኮሊስትሮል፣ የደም ግፊት፣ የስኳር እና የክብደት መጨመር ላይ ቅድመ ክትትል የማድረግ ሥራ እንዲሠሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ይሰጣል። ችግሩ ያለባቸው ሰዎችም ክትትል እንዲያደርጉ እየተደረገ መኾኑን ነግረውናል።
በሽታውን ለመከላከል ጤና ተቋማት በተደራጀ መንገድ ቅድመ መከላከል ላይ ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው መክረዋል። ማኅበረሰቡ ክትትል እንዲያደርግ መንግሥት ደግሞ መመርመሪያ ማሽኖችን በጤና ተቋማት ማሟላት እንዳለበትም መክረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!