ማኅበረሰቡ በዓልን ተከትሎ ሊከሰቱ ከሚችሉ አደጋዎችና ወንጀሎች እንዲጠነቀቅ የደብረ ብርሃን ከተማ ፖሊስ መምሪያ አሳሰበ።

24

ደብረ ብርሃን: ሚያዝያ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የትንሣኤ በዓል ከድንገተኛ አደጋ የጸዳ ኾኖ እንዲያልፍ ማኅበረሰቡ አስፈላጊውን የበዓል ጥንቃቄ እንዲያደርግ የደብረ ብርሃን ከተማ ፖሊስ መምሪያ አሳስቧል። በመምሪያው የሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ዋና ክፍል ኀላፊ ኮማንደር ኪዳኔ በቀለ ፖሊስ የሕዝቡን ደኅንነት ለማረጋገጥ እየሠራ ነው ብለዋል።

በዓሉን ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ ድንገተኛ አደጋዎችን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል ፖሊስ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ስለመኾኑም ተናግረዋል። የሀሰተኛ ብር ዝውውር ሊኖር ስለሚችል ማኅበረሰቡ ግብይት ሲፈጽም ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ነው ያሳሰቡት። ትልልቅ ግብይቶችንም በባንክ በኩል የገንዘብ ዝውውር ማድረግ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

በዓላቱን ተከትሎ በምግብ ዝግጅት ወቅት ሊፈጠር የሚችል የእሳት አደጋን ለመከላከል ማኅበረሰቡ በጥንቃቄ ማብሰል አለበት ሲሉም አሳስበዋል ኮማንደር ኪዳኔ፡፡ ችግር ሲያጋጥም በፍጥነት ለፖሊስ መረጃ በመስጠት መቆጣጠር እንዲቻል ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። ፖሊስ በተለያዩ ማዕከላት አደረጃጀቶችን በመፍጠር ሰላም እና ደኅንነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሠራ መኾኑን የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዋና ክፍል ኀላፊው ተናግረዋል።

በቅዳም ስዑር ማኅበረሰቡ ከተለያዩ አካባቢዎች ተሰብስቦ ግብይት ይፈጽማል ያሉት ኮማንደር ኪዳኔ በግብይት እና በጉዞ ወቅት የሥርቆት ወንጀል እና የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡- ኤልያስ ፈጠነ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሦስት ሠዓት አይሁድ ኢየሱስ ክርስቶስን ይሰቀል! ይሰቀል! ይሰቀል! ያሉበት ሰዓት ነው”
Next articleየፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ-ግብረ ኃይል የትንሣዔ በዓል በሰላም እንዲከበር ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ።