“ሦስት ሠዓት አይሁድ ኢየሱስ ክርስቶስን ይሰቀል! ይሰቀል! ይሰቀል! ያሉበት ሰዓት ነው”

114

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርቶስ በሰሙነ ሕማማት ሐሙስ ለአርብ አጥቢያ በአይሁድ እጅ ከመያዙ በፊት የአይሁድን እግር አጠበ፣ ሃዋርያትን እራት አበላቸው፣ ስለመንፈስ ቅዱስ የሚያጽናና ትምህርት አስተማራቸው፣ አልለያችሁም፣ ከእናንተ ጋር ነኝ እያለም አስተምሯቸዋል፡፡

በጌቴሰማኒ ባስተማረው ሰፊ ትምህርትም ወደፈተና እንዳትገቡ ትጉና ፀልዩ ብሏቸው ነበር፣ እርሱም ስለራሱ ጸለየ። ከዚያም ለአይሁድ ተላልፎ ተሠጠ። አይሁድም ሌሊቱን ሲገርፉት ሲያሰቃዩት አደሩ ይላሉ በጽርሐአርያም ደብረ ሲና በዓታ ለማርያም አንድነት ገዳም የስብከተ ወንጌል ኀላፊ መምህር አብርሃም ሞላ።

አይሁድ ለምን ክርስቶስን መስቀል ፈለጉ?
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቲዎስ ወንጌል ምዕራፍ 20 ላይ “ቤቴ የጸሎት ቤት ናት” ብሎ ነበር፤ አንድም ቤቴ የጸሎት ቤት ኾና እያለ ስለምን የገበያ አዳራሽ ታደርጉታላችሁ ብሎ እየገረፈ አስወጥቷቸው ነበርና፤ ሁለትም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም በመጣ ጊዜ ሙታንን አስነስቷል፣ ለምጻሙን አንጽቷል፣ አንካሳውን ጠግኗል፣ ህሙማንን ፈውሷል።

ወደ መጠመቂያው ስፍራ በወረደ ጊዜ ለ36 ዓመት የታመመውን ”መጻጉን” አግኝቶት “መዳን ትፈልጋለህ” አለው። መጻጉም “አዎ” መዳን እፈልጋለሁ አለው። አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ብሎት ነበር፡፡ መጻጉ የጥቅል ስም ነው፡፡ በመጻጉ ስም የተጠሩ በርካታ ህሙማን ነበሩ የተፈወሱ፡፡

መጻጉ የተፈወሰባት ቀን ቀዳሚት ሰንበት ነበረች። አይሁድ ቀዳሚት ሰንበትን ካጠፉ ሳይዘረጉ፤ ከዘረጉ ሳያጥፉ ያከብሯት ስለነበር ኢየሱስ ክርስቶስ በቀዳሚት ሰንበት ህሙማንን ስለፈወሰ አጥብቀው ጠልተውት ነበር። ለዚህም ለማስወገድ ተስማሙ። ይህ ሰው ከሴት እንደተወለደ እያወቅን ከአብ ከአባቴ የተላክሁ ነኝ ይላል። የአይሁድ ንጉሳቸው ነኝ ይላል ብለው ጠሉት ይላሉ መምህር አብርሃም።

አርብ ሦስት ሰዓት ላይ የኢየሱስ ክርስቶስ እንግልቱ ተጠናክሮ የቀጠለበት ሰዓት ነው። በጲላጦስ አደባባይ ተገኝቶ የከፋ ግርፋት ተገረፈ።
ሌሊት ከሃና ወደ ቀያፋ ወሰዱት፤ ከቀያፋ ወደ ሃናም መለሱት። ቀያፋ የብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት ነበር። ሃና አርጅቶ ስለነበር ቀያፋን ልጁን አጋብቶ ሊቀ ካህናት አድርጎ ሾሞት ነበር። ክርስቶስን ለሞት ያበቁት እነዚህ ሁለት ሊቀ ካህናት ናቸው። ምክንያቱም ምድራዊ ንጉስ መስሏቸው፣ ሥልጣናቸውን የሚቀማቸው መስሏቸው ነበር። እነሱም ወደ ጲላጦስ እንዲወስዱት አዘዙ።

ጲላጦስም በደልም ሀጢያትም አላገኘበትምና ወደ ሄሮድስ ውሰዱት አላቸው። ሄሮድስም “አንተ ነህ የአይሁድ ንጉሳቸው?” ብሎ ሲጠይቀው ኢየሱስ ክርስቶስም ዝም አለ። ዝምታው ስለ ሁለት ነገር ነበር ይላሉ መምህሩ። አንድም ትህትናን ለማስተማር ሲኾን ሁለትም ሰሚ በሌለበት መናገር አያስፈልግም ሲል ነው። ሄሮድስ ግን በዚህ ዓለም ታይቶ የማይታወቅ ግርፋትን አስገረፈው ቀይ ከለሜዳ አለበሰው። ክርስቶስም ነገ የሚፈስሰው ደሜ ነው ሲል ቀይ ከለሜዳ ለበሰ። አንድም ነገ ጥጦስ የሚባል ጨካኝ ንጉስ መጥቶ እስራኤላውያንን ያጠፋችኋል ሲል ነው ብለዋል መምህሩ።

ሄሮድስም አንተስ ሁለት ሞት ይገባሃል አለው እና ወደ ጲላጦስ ውሰዱት አላቸው። ከጲላጦስ ሲደርስ የጲላጦስን ደጃፍ የሚጠብቁ ስድስት ኃያላን ወታደሮች ነበሩ። ወታደሮቹ ለጌታችን ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰገዱ፣ ጲላጦስም ወታደሮቹ እንዳይሰግዱ በ10 ወታደር አስያዛቸው። አልቻሉም፣ በ15 ወታደሮች አስያዛቸው አሸንፈው ሰገዱለት በዚህ ጊዜ ጲላጦስ ደነገጠ። አከታትላም ሚስቱ መልዕክተኛ ላከች “በዚህ ጻዲቅ ሰው ላይ እጅህን እንዳታነሳ፣ ምንም ፍርድ እንዳትፈርድ” ብላ መናገር እና መስማት የማይችሉት ሁለቱ ልጆቿ የነገሯትን አስነገረችው።

ጲላጦስም “አንተ የአይሁድ ንጉስ ነህ” አለው “እሱንስ አንተ አልክ” አለው ኢየሱስ ክርስቶስ። በዚህ ጊዜ ልሰቅልህም፣ ልገርፍህም፣ ልገድልህም እንደምችል ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅምን ባለው ሰዓት “ከላይ ከሰማይ ከአባቴ ካልተሰጠህ በቀር እኔ ላይ ይህን የማድረግ ሥልጣን የለህም” አለው። ይህን የሰማው ጲላጦስ ከዚህ ንጹህ ሰው ደም ንጹህ ነኝ ብሎ ውኃ አስመጥቶ እጁን ታጠበ። ሕዝቡ ግን ጥላቻው አይሎ ሥለነበር ግርፋት አይበቃውም ይሰቀል፣ ይሰቀል፣ ይሰቀል ይሉት ነበር።

አይሁድ የፋሲካን በዓል ሲያከብሩ ሰው የመስቀል ልማድ ነበራቸው እና ወንበዴውን በርባንን ልስቀልላችሁ ክርስቶስ ግን ገርፌ ልልቀቀው አላቸው። የለም ክርስቶስ ይሠቀል በርባንን ግን ፍታልን አሉት።
አይሁድ ጥላቻቸው ከእለት ወደ ዕለት እያየለ መጥቷል። በእለተ ሆሳዕና ሕጻናት እና አረጋውያን ዘንባባ እና የለበሱትን ጋቢ እያነጠፉ ሆሳዕና በአርያም ለወልደ እግዚያብሔር ልጅ እያሉ የቢታንያ ድንጋዮች ሳይቀሩ መዘመራቸው ያናደዳቸው አይሁዳውያን ሕዝቡን አሳድመው፣ አሳምጸው ይሰቀል ዘንድ ፈረዱበት። ንጹሃ ባሕሪ እግዚአብሔርም በፈጠረው ፍጥረት መከራን እንዲቀበል ኾነ ይላሉ መምህር አብርሃም በማብራሪያቸው።

ሀጢያት የሌለበት ክርስቶስ እንደ ሀጢያተኛ ተገፋ፣ ተዳፋ፣ ተገረፈ፣ ተሠቀለ ይላሉ። በመጨረሻም ከጲላጦስ አደባባይ ወደ ቀራንዮ ከሰባት እጽ የተሠራውን መስቀል አሸክመው እያዳፉ ወሰዱት።
አንድ ሰዓት አዳም አባታችን የተፈጠረበት ሠዓት ሲኾን አርብ ሦስት ሰዓት እናታችን ሄዋን የተፈጠረችበት ሰዓት ነበር። በእነዚህ ሰዓታት ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእነሱን በደል ለመሻር ሲል መከራን ተቀበለባቸው ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየበዓል ወቅት የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት እየሠራ መኾኑን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ።
Next articleማኅበረሰቡ በዓልን ተከትሎ ሊከሰቱ ከሚችሉ አደጋዎችና ወንጀሎች እንዲጠነቀቅ የደብረ ብርሃን ከተማ ፖሊስ መምሪያ አሳሰበ።