
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የበዓል ወቅት የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ከ4 ሺህ ኩንታል በላይ የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርቶችን ለሸማቾች በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረቡን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ አስታውቋል። የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ንግድ እና ገብያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ያረጋል ያየህ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ የግብዓት አቅርቦት እጥረት እንዳያጋጥም በልዩ ትኩረት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በሚገኙ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል ከ4 ሺህ ኩንታል በላይ የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርቶች እንዲሁም 20 ሺህ ሊትር ዘይት በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረቡን መምሪያ ኀላፊው ገልጸዋል። የዳቦ ዱቄት፣ ዘይት፣ ስኳር፣ ጤፍ፣ ሽንኩርት፣ እንቁላል እና ሌሎችም ከቀረቡ ግብዓቶች መካከል እንደሚገኙበት ተገልጿል።
ከእንስሳት ተዋጽኦ ግብይት ጋር ተያይዞ ሊፈጠር የሚችለውን የአቅርቦት እጥረት ለመፍታት አምራቾችን ከሸማቾች ጋር የማትስተሳሰር ሥራ መሠራቱንም ኀላፊው አንስተዋል። ሸማቾች በበዓላት የግብይት ወቅት ሊፈጠሩ ከሚችሉ የማጭበርበር ወንጀሎች እራሳቸውን እንዲጠብቁም መምሪያ ኀላፊው አሳስቧል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!