ሆ! ሚሻሚሾ

60

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል ሰሞን ከሚከበሩ እና ከሚዘከሩ በዓላት መካከል በዕለተ አርብ የሚከበረው ስቅለት አንዱ ነው። በዚህ ቀን ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ድኅነት ሲል ተሰቅሎ ቅዱስ ነፍሱ ከቅዱስ ሥጋው የተለየበት የጭንቀት እና የሐዘኔታ ጊዜ ይዘከራል። በዚሁ ዕለት ማለዳ ደግሞ ሕጻናት ”ሚሻሚሾ” ተብሎ በሚጠራው ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ክዋኔ ደምቀው ያረፍዳሉ።

በፈለገ ግዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም መምህር ዮሴፍ ዳኘው የሚሻሚሾን ሃይማኖታዊ ዳራ፣ ባሕላዊ ትውፊት እና ማኅበረሰባዊ ጠቀሜታ ለአሚኮ ተናግረዋል። ሐሙስ የቂጣ በዓል ተከብሮ በማግስቱ አርብ ክርሥቶስ መሰቀሉን ያስታወሱት መምህር ዮሴፍ ወቅቱ የቂጣ በዓል በመኾኑ መነሻውም እስራኤላውያን በግብጽ 215 ዓመት ቆይተው ሲወጡ ይዘውት የወጡት በዓል እና በየዓመቱ የሚያከብሩት እንደኾነ ነው የገለጹት።

መምህር ዮሴፍ ስለሚሻሚሾ በሃይማኖት መጻሕፍት የተጻፈ ነገር ባይኖርም ሕጻናት ሚሻሙሾ ወይም ኦሚሻሙሾ የሚሉት አይሁዳውያን ክርስቶስን ሲይዙት እና ሲሰቅሉት ‘ውሾ ውሾ’ ብለው ሰድበውት እና ዘብተውበት ስለነበር ያንን ለማስታወስ እንደኾነ በቃል ይነገራል ብለዋል። ሕጻናቱ ሚሻሙሾ በማለት በየቤቱ በር ግጥም ሲደረድሩ የሚይዙት የተዥጎረጎረ እና ጫፉ የሾለ ዱላ ደግሞ አይሁዳውያን ክርስቶስን በያዙት ጊዜ ይዘውት የነበረውን ሾተል እና ጎመድ ለማሰብ መኾኑን ገልጸዋል። ጥቁር እና ነጭ ኾኖ የተዥጎረጎረው ቀለም በአንድ ዱላ ላይ መኾኑም የክርሥቶስን የመለኮት እና የሥጋ ባሕርይ መኖር ለመግለጽ ነው ብለዋል።

ሐሙስ የቂጣ በዓል ሲኾን በማግሥቱ ዓርብም ሕጻናቱ በየሰፈሩ እየዞሩ ሚሻሙሾ በማለት ቂጣ ይቀበላሉ። በየቤቱ እየዞሩ ዳቦ እና ሌሎች ምግብ ነክ ነገሮች ሲለምኑም ከሚሏቸው ስንኞች መካከል፦

”እማማ ይነሱ
ጉሽጉሻ ይዳብሱ

ከአደረው ዱቄት ትንሽ ይፈሱ” የሚሉት ይጠቀሳሉ።

በባሕር ዳር ከተማ የሽንብጥ ሠፈር ሕጻናት ተሰባስበው ሚሻሚሾን በየዓመቱ ይዘክራሉ። ትንሽ እና ትልቅ ድሃ እና ሃብታም ሳይለዩ ተሰባስበው በየቤቱ እየዞሩ የሚሻሚሾን ዜማ እና ግጥም በመደርደር ምግብ ነክ ነገሮች ይለምናሉ። ወላጆችም ዱቄት፣ ሽሮ፣ በርበሬ እና ዘይት ይሰጧቸዋል።

የዘንድሮውን የሚሻሚሾ ቡድን በማቀንቀን ሲመራ ያገኘነው ሕጻን ሳሙኤል ኃይሉ በዓሉ በየዓመቱ ሲመጣ ደስተኛ እንደኾኑ እና በጋራ ሚሻሚሾ ብለው ጨፍረው የሚያገኙትን ምግብ አስበስለው በጋራ እንደሚመገቡ ተናግሯል። በጭፈራቸውም፦

ሆ! ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
አንድ አውራ ዶሮ
እግሩን ተሰብሮ
እዘኑለት
ስላውዳመት
እሜቴ ይነሱ
ይወሳወሱ

ካደረው ዱቄት ትንሽ ይፈሱ። በማለት ዱቄት ይቀበላሉ። ቀጥሎም፦
ጨውጨው ማጣፈጫው
ዘይት ዘይት መሰልቀጫው።
በማለት በርበሬ እና ዘይት ይቀበላሉ። ከዓመት ዓመት ያድርስልን ብለው አመስግነው ወደ ቀጣዩ ቤት ለተመሳሳይ ጭፈራ ይሄዳሉ። ሚሻሚሾ ከሃይማኖታዊ ፋይዳው በተጨማሪ ያለውን ባሕላዊ ጠቀሜታም መምህር ዮሴፍ አብራርተዋል። ሃይማኖት ቀኖናን ያመጣል፤ ቀኖና ደግሞ ሥርዓት አለው፤ ከሥርዓት ትውፊት፤ ከትውፊት ሃይማኖታዊ ባሕል በመኾን እንደሚሰናሰል ገልጸዋል። ”ይህ ባሕል ለሰዎች ጠቃሚ መኾን አለበት፤ ሰላም፣ አንድነታቸውን የሚያጠናክር፣ የሥራ ባሕላቸውን የሚያዳብር፣ መረዳዳትን እና አብሮ መብላትን የሚያመጣ ከኾነ መነሻው ከሃይማኖት የመጣ ባሕል ነው ማለት ነው” ብለዋል። ሕጻናት ሲሰበሰቡ አንድ ላይ መኾናቸውን ያውቃሉ፤ ፍቅር ይኖራቸዋል። በዚያ ላይ ሁሉም አብረው ይሠራሉ፤ አብረው ነው ሚሻሚሾ እያሉ የሚለምኑት። ይህ አብሮ መለመን አብሮ መሥራትን፣ በጋራ ሲበሉ ደግሞ አንድነትን ነው የሚማሩት። አብሮ መሥራት እና አብሮ መብላት ካለ ሀገር ሰላም ነው የሚኾነው ሲሉም ባሕላዊ ጠቀሜታውን አመላክተዋል።

በሀገራችንም ኾነ በዓለም ሁሉም በጋራ ሠርቶ በጋራ ቢበላ ጥሩ ነው ያሉት መምህር ዮሴፍ በአሁኑ ጊዜ መሥራትም መብላትም ለየብቻ እየኾነ እንደሄደ ገልጸዋል። እንደዚያ ሲኾን ደግሞ ሀገር እንደማያድግ፣ ሰላምም፣ ፍቅርም፣ ጥንካሬም እንደማይኖር ጠቅሰዋል። ሕጻናቱ ከሚከውኑት በጋራ ሠርቶ በጋራ የመብላት የአንድነት እና የፍቅር ማሳያ ብሂል ከኾነው ከሚሻሚሾ ሥርዓት መማር እንደሚገባም መክረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በአማራ ክልል ሰላም በመስፈኑ ለልማት ሥራዎች ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል” አቶ አደም ፋራህ
Next articleየበዓል ወቅት የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት እየሠራ መኾኑን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ።