
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ማሥተባበሪያ ማዕከል ኀላፊ አደም ፋራህ ከአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች ጋር በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ የሚከናወኑ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
አቶ አደም ፋራህ “በአማራ ክልል ሰላም በመስፈኑ ለልማት ሥራዎች ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል” ብለዋል። የክልሉ ሕዝብ ሰላም እንዲመለስ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የፀጥታ መዋቅር ከፖለቲካ አመራሩ ጋር በመኾን ከፍተኛ ሥራ ማከናወናቸውንም ገልጸዋል። አሁን ላይ ክልሉ የተሻለ ሰላም ማግኘቱን ገልጸው ይህም ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነው ብለዋል።
አሁን ላይ ከክልሉ ጀምሮ የዞን እና የወረዳ አመራሮች የአካባቢያቸውን ሰላም በቁርጠኝነት እያስከበሩ የልማት ሥራዎችንም በከፍተኛ ተነሳሽነት እያከናወኑ እንደሚገኙ ተመልክተናል ብለዋል አቶ አደም። በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ በርካታ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መኾናቸውንም ጠቁመዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ ውስጥ የሌማት ቱሩፋት ሥራዎች በስፋት እየተሠሩ እንደሚገኙ መመልከታቸውንም አቶ አደም ፋራህ ገልጸዋል። የዓሣ እርባታ፣ ከብት ማድለብ፣ ዶሮ እርባታ እና ሌሎችም የእንስሳት ዘርፍ ሥራዎች በሰፊው መከናወናቸው ሀገሪቱ የያዘችውን የሌማት ቱሩፋት እንቅስቃሴ የሚደግፍ ነው ብለዋል። ወጣቶችንም ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አምራች ኢንዱስትሪዎች እንደ ሀገር ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጣቸው ናቸው ያሉት አቶ አደም በአማራ ክልል በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎች ሥራቸውን እያከናወኑ ነው ብለዋል። ለአብነትም በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ የተመለከቱት ግዙፍ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለሀገሪቱ የእንስሳት ሃብት እድገት ጉልህ ሚና የሚጫወት ስለመኾኑም ተናግረዋል።
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የእንስሳት መኖ ችግር አለ፤ ይህም የዘርፋ ማነቆ ነው ብለዋል አቶ አደም። በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘው የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ከአካባቢው አልፎ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎችም ምርቱን በማዳረስ እና ችግሩን በመፍታት የሌማት ቱሩፋት ሥራዎችን ማገዝ የሚችል ስለመኾኑም ገልጸዋል።
አቶ አደም ፋራህ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ በተጨማሪ ምርት ወደ ጎረቤት ሀገራት በመላክ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ለመኾን አሥቦ መሥራት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል። ለዚህም የገበያ ትስስርን ማጠናከር ተገቢ ነው ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!