
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የፌዴራል እና የአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ የሚከናወኑ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል። ምልከታውን ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ማሥተባበሪያ ማዕከል ኀላፊ አደም ፋራህ፣ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎችም የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች ናቸው።
ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ባሕር ዳር ከተማ ሰፊ የልማት እንቅስቃሴ የሚካሄድባት ከተማ መኾኗን ገልጸዋል። ስለባሕር ዳር ከተማ በርቀት የሚወራው ሌላ ነው፤ እውነቱ ሲመዘን ግን ሰላሟን አስጠብቃ ሕዝቦቿም በመደበኛ የልማት ሥራ ላይ ናቸው ብለዋል። በከተማዋ ዓሣን ጨምሮ የተለያዩ እንስሳት እርባታ እየተካሄደ ነው፤ በአትክልት እና ፍራፍሬ ዘርፍም በከተማዋ ዙሪያ የሚገኙ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ስለመኾናቸው ከፍተኛ መሪዎቹ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ባሕር ዳር ሰፊ የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ እየተካሄደባት ነው፤ ከክልሉ አልፎ ለሌሎችም የሚተርፍ የፋብሪካ ምርት የምታቀርብ ከተማ ናት ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ። በመሠረተ ልማት ግንባታ ዘርፍም በርካታ መልካም ተሞክሮዎች ያሏት ከተማ ስለመኾኗ ገልጸዋል። ለአብነትም ከተማዋን የሚመጥኑ ዘመናዊ የመንገድ መሠረተ ልማቶች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አንስተዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ከዳር አድርሶ ተጨማሪ እና የተሻሉ የልማት ሥራዎችን ለመጀመር ሰላም የማይተካ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል። “ሰላም ለልማት ትልቅ ቅድመ ኹኔታ ነው፤ ልማትም ለሰላም መሠረት ነው” ሲሉ የሰላም እና የልማትን ተመጋጋቢነት ገልጸዋል። አቶ አረጋ “ጦርነት እና ግጭት የመጨረሻዎቹ የጥፋት መንገዶች ናቸው፤ ግጭት ቀስቃሾች ከጥፋት መንገድ መቆጠብ አለባቸው” ብለዋል። መንግሥት ለሰላም ሁሌም በሩ ክፍት ነው፤ የሰላም ጥሪም በተደጋጋሚ እያደረገ ነው ብለዋል። የሰላምን ጥሪውን ከመቀበል ይልቅ አሁንም ቃል እየመረጡ በመወርወር ሕዝብን ለማጋጨት መንቀሳቀስ እንደ ግለሰብ አክሳሪ ነው፤ እንደ ማኅበረሰብም ይጎዳል ነው ያሉት።
መንግሥት ሕግ የማስከበር ኀላፊነቱን በመወጣት የኅብረተሰቡን ሰላም እንደሚያስጠብቅም ገልጸዋል። የሰላም ጥሪው በግጭቱ ለተሳተፉ አካላት ከማኅበረሰቡ ጋር በሰላም ለመኖር አማራጭ የሌለው ምርጫ እና ትልቅ እድል ስለመኾኑም ተናግረዋል። ግጭት የገንዘብ ምንጫቸው የኾነ እና ያለግጭት መኖር የማይችሉ አካላት የሚያደርጉትን የጥላቻ ቅስቀሳ ጆሮ በመንሳት ሰላምን መምረጥ እና ሙሉ ጊዜን በልማት ላይ ማዋል እንደሚገባም ርእሰ መሥተዳድሩ አሳስበዋል።
የሚያስፈልገው ሰላሙ ተጠብቆ ለሀገር እድገት አስተዋጽኦ የሚያደርግ፣ የለማ፣ ሃብት የፈጠረ እና ተወዳዳሪ ሕዝብ መፍጠር ነው ብለዋል። ይኽ እንዲኾን ደግሞ ሕዝቡ ከመሪዎቹ ጋር ተባብሮ በመሥራት የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት አሳስበዋል። ርእሰ መሥተዳድሩ የክልሉ አመራሮች የሕዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ ቁርጠኛ ሥራ እያከናወኑ ስለመኾናቸውም አረጋግጠዋል። ማኅበረተሰቡም እየተመካከረ በየአካባቢው የራሱን ሰላም በማስጠበቅ የልማት ተሳታፊ መኾን እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!