
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ማስተባበሪያ ማዕከል ኀላፊ አደም ፋራህ ከአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች ጋር በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ የሚከናወኑ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል።
መሪዎች ከተመለከቷቸው የመሠረተ ልማት ግንባታዎች መካከል በባሕር ዳር ከተማ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ሊደረግ ቀናት የቀሩት የዓባይ ወንዝ ድልድይ፣ የተለያዩ አምራች ኢንዱስትሪዎች እና የሌማት ቱሩፋት ሥራዎች ይገኙበታል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በባሕር ዳር ከተማ የሚሠሩ የልማት ሥራዎች ከአካባቢው ሕዝብ በተጨማሪ ለሀገርም ትልቅ ጸጋ ናቸው ብለዋል።
ከተማዋ የጣና እና የዓባይን ጸጋ ተጠቅማ እየለማች ያለች ከተማ ስለመኾኗም ገልጸዋል። አቶ ተመስገን የጎርጎራ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት እና ውብ የኾነው የዓባይ ድልድይ በቅርቡ እንደሚመረቁ ጠቁመው ለባሕር ዳር ሕዝብ ብሎም ለሀገር ትልቅ የቱሪዝም ቱሩፋት እንደሚያስገኙ አብራርተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ባሕር ዳር ዓባይ በጣና ላይ አቋርጦ የሚጓዝባት፣ በጣና ሐይቅ ላይ በርካታ ደሴቶች የታጀበች እና ምቹ የአየር ንብረቷ ከትልልቅ ፕሮጀክቶች ጋር ተደማምሮ የቱሪስት መዳረሻነት አቅሟን ከፍ እንደሚያደርገውም ገልጸዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሌማት ቱሩፋት አንዱ ክፍል ኾኖ በድልድዩ ዙሪያ በወጣቶች የሚለማውን የዓሳ ማራቢያ ኩሬም ጎብኝተው ወጣቶቹን አበረታትተዋል።
በከተማዋ ከሚገኙት አምራች ኢንዱስትሪዎች ውስጥም ግዙፉን ሙሌ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ እና የዓባይ ዘይት ፋብሪካን የሥራ አንቅስቃሴ ተመልክተዋል። ሙሌ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገጥመውን የእንስሳት መኖ እጥረት በመቅረፍ ለዘርፉ ትልቅ እድገት የሚያስገኝ ስለመኾኑ ጠቁመዋል። ፋብሪካው የገጠመው የማምረቻ ቦታ እጥረት በአግባቡ ተፈትቶ የበለጠ እንዲያመርት መሥራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
አቶ ተመስገን “ሕዝቡ ሰላም እና ልማት ነው የሚፈልግ” ሲሉ ተናግረዋል። ተገንብተው ከተጠናቀቁ እና ገና ከሚጀመሩ ሰፋፊ የልማት ሥራዎች ተጠቃሚ ለመኾን የአካባቢውን ሰላም መጠበቅ እና ማጽናት እንደሚገባም አሳስበዋል። ችግሮች ቢከሰቱ እና ጥያቄዎች ቢኖሩ እንኳን በሰለጠነ አግባብ በጠረጼዛ ዙሪያ እየተወያዩ የመፍታት ባሕልን ማዳበር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!