
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ በባሕር ዳር ከተማ የተከናወኑ የሌማት ትሩፋት ሥራዎች ስኬታማ መኾናቸውን ገልጸዋል።
አቶ ተመሥገን በባሕር ዳር ከተማ ዘርፈ ብዙ ልማቶች መመልከታቸውን ጠቅሰዋል። እነዚህ ልማቶች በተገኘው ሰላም ውስጥ መከናዎናቸውን በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው አሥፍረዋል።
ሙሉ መልእክታቸው ቀጥሎ ቀርቧል፦
ባሕር ዳር መልክ አትፈጅም ይሏታል፤ ሊያሣምራት፣ ሊያስውባት እና አዲስ መልክ ሊሠጣት ላሰበ ለማንም የምትመች ቆንጆ መልክዓ ምድር ያላት ውብ ተፈጥሮ ናት።
ዛሬ በዚህች ከተማ የተመለከትነው የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር እጅግ አስደንቆናል። ከብት ማድለብ፣ ዶሮ፣ እንቁላል፣ ወተት፣ መኖ ፋብሪካ፣ ዓሳ፣ የጓሮ አትክልት እኚህ ሁሉ በሌማት ትሩፋቱ የተገኙ የጥረት ውጤቶች ናቸው፡፡
ማዕድ ሞልቶ ማየት፤ ምግብ ከሌማቱ ተትረፍርፎ መመልከት የሀገር ሰውን ልብ ያሞቃል፡፡ በባሕር ዳር የሆነውም ይኸው ነው፡፡ በባለ ብዙ ጸጋ ባለቤት በሆነችው ውቢቷ ባሕር ዳር ከተማ ጸጋዋን ወደ ሁለንተናዊ ልማት የሚቀይሩ የሌማት ትሩፋት ስራዎች ጥሩ ጅምር ላይ መሆናቸው ደግሞ እጅግ አስደሳች ነው፡፡
በሌላ በኩል አዲሱ የዓባይ ወንዝ ድልድይ የመጨረሻ ምዕራፍና የመንገድ ግንባታዎች በአጭር ጊዜ ተጠናቀው አገልግሎት ይጀምራሉ፡፡ ይህም የከተማዋን ዘመናዊነትና የቱሪስት ተደራሽነት በእጅጉ ይጨምረዋል፡፡
የገበታ ለሀገር አካል የሆነው የጎርጎራ ፕሮጀክት ሌላኛው የክልሉን የቱሪስት መዳረሻነት የሚያሳድገው ድንቅ ሀሳብ ሲሆን ለዚህም የሀገር ሃብት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ስካይ ላይት ሆቴል የአስተዳደር ኀላፊነቱን እንዲወስድ መንግሥት ውሳኔ አሳልፏል፡፡
የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት የሚያመላክተን ሰላም የሁሉ መሰረት መሆኑን ነው። ሕዝብ ልማትን፣ ዕድገትና ብልጽግናን ይፈልጋል። ለጥያቄዎችና ልዩነቶች ውይይት፣ምክክርና መደማመጥን ያስቀደመ አካሄድ ደግሞ ሁሉም የሚያተርፍበት አካሄድ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!