ኢራቅ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች።

60

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ እና የኢራቅ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ የሁለትዮሽና ዘርፈ ብዙ ግንኙነትን ለማጠናከር እንደሚሠሩ በኢራቅ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሰኢድ ሙሁመድ ጅብሪል (ዶ.ር) ገልጸዋል። ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሰኢድ ሙሁመድ ጅብሪል (ዶ.ር) በባግዳድ በሚገኘው ሰላም ቤተ መንግሥት በተካሔደ ሥነ-ሥርዓት ላይ በመገኘት የሹመት ደብዳቤያቸውን ለኢራቅ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት አብዱለጢፍ ጀማል ረሽድ (ዶ.ር) አቅርበዋል።

አምባሳደሩ በወቅቱ እንዳሉት በኢትዮጵያ እና ኢራቅ ረዥም ዘመናት ያስቆጠረውን የሁለትዮሽና ዘርፈ ብዙ ግንኙነት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በኢነርጂ፣ ባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። የኢራቅ መንግሥት በድጋሜ በኢትዮጵያ ኤምባሲውን ለመክፈት ላደረገው ተነሳሽነት ምስጋና በማቅረብ የኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄውን መቀበሉንና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ዝግጁነትም አብራርተዋል።

አምባሳደሩ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለኢራቁ ፕሬዝዳንት አብዱላጢፍ ጀማል ረሽድ(ዶ.ር) የላኩትን መልዕክትና መልካም ምኞት አድርሰዋል። የኢራቁ ፕሬዚዳንት በበኩላቸው ኢራቅ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የኢራቅ መንግሥት በኢትዮጵያ በድጋሚ ኤምባሲውን ለመክፈት አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁንና በኢትዮጵያም በኩል ተቀባይነት ማግኘቱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዞኑን ሕዝብ የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስታወቀ፡፡
Next article“ለጥያቄዎችና ልዩነቶች ውይይት፣ ምክክርና መደማመጥን ያስቀደመ አካሄድ ሁሉም የሚያተርፍበት ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ