
ደብረ ማርቆስ: ሚያዝያ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዞኑን ወቅታዊ የሰላም ሁኔታ፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች በተመለከተ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ዋለ አባተ ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ የፀጥታ ኀይሉ ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ በሠራው ሥራ በዞኑ አንጻራዊ ሰላም እየታየ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
በዞኑ የሰላም ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ በመምጣቱ በተለያዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የልማት ዘርፎች ላይ ሰፊ እንቅስቃሴ እተደረገ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ዞኑ ትርፍ አምራችነቱ የሚታወቅ በመኾኑ የመኸር እርሻን ውጤታማ በኾነ መልኩ ለመፈጸም ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ምክትል አሥተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡
ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ አርሶ አደሮች መንደር ለማድረስ እየተሠራ መኾኑንም ምክትል አሥተዳዳሪዉ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ እስካሁን ከ5 መቶ ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ወደ መሰረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራት መሰራጨቱን ነው የተናገሩት፡፡
ለዞኑ ከሚያስፈልገው ከ30 ሺህ ኩንታል በላይ የበቆሎ ምርጥ ዘር ውስጥ እስካሁን አንድ ሦስተኛዉ መቅረቡን እና ከዚህም ውስጥ 76 በመቶ የሚኾነውን ለአርሶ አደሮች ማሰራጨቱን ገልጸዋል፡፡
እንደ ምክትል አሥተዳዳሪው ገላጻ ግጭቱ ከፍተኛ ጫና ያሳደረበት የገቢ አሰባሰብ ዘርፉ ሲሆን ለመሰብሰብ ከታቀደው ሦስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ውስጥ እስካሁን ማሳካት የተቻለው 27 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይህን ዝቅተኛ አፈጻጸም ለማሻሻል አንጻራዊ ሰላም በሚታይባቸው አካባቢዎች እስከ ቀበሌ ድረስ ወርዶ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም አብራርተዋል፡፡
ምክትል አሥተዳዳሪው እንዳሉት ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የትምህርት ዘርፉ ተጠቃሽ ነው፡፡ በዞኑ የሰላም እጦት በትምህርት ዘርፉ ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖውን እንዳሳረፈም ነው የገለጹት፡፡ ይህም በተማሪዎች ላይ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጫና እያሳደረ ይገኛል ነው ያሉት፡፡ ያም ኾኖ ከሰላም ማስከበር ተግባራት ጎን ለጎን የትምህርት ሥራዎችን ለማስጀመር ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በዞኑ 42 ትምህርት ቤቶች አስቀድመው ወደ መማር ማስተማር ሥራቸው የገቡ ሲሆን በ11 ወረዳዎች በ64 የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ የመማር ማስተማር ሥራውን ለማስጀመር እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ በዞኑ ከሰላም እና ሕግ ማስከበር ጎን ለጎን አንገብጋቢ በኾነው የጤና ዘርፍ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለማቃለል እና አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ምክትል አሥተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡
በፀጥታ ችግሩ ምክንያት የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም እና የመድኃኒት አቅርቦት ችግርን ለማሻሻል በልዩ ትኩረት እየተሠራ መኾኑን ምክትል አሥተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡ በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን በዞኑ በእቅድ ከተያዘው ከ500 ሺህ በላይ አዲስ እና ነባር አባላት መከከል ከ160 ሺህ በላይ የሚኾኑትን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡ በጤና መድኅን አገልግሎት ገቢ አሰባሰብ ረገድም እስካሁን ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ነው ያብራሩት፡፡
ኅብረተሰቡን በማወያየት እና የሰላም ባለቤት በማድረግ የልማት ተጠቃሚ እንዲኾን ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡ ምክትል አሥተዳዳሪው ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክትም አሥተላልፈዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!