የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ለ136 ማኀበራት የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ አስረከበ።

15

ጎንደር: ሚያዚያ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከተማ እና መሠረተ ልማት ዋና ሥራ አሥኪያጅ አንዱዓለም ሙሉ እንደገለጹት በማኅበራት ተደራጅተው የቤት መሥሪያ ቦታ ለተወሠነላቸው 136 ማኅበራት ከ100 ሄክታር በላይ መሬት ርክክብ ማድረጉን ገልጸዋል። ይኽም የ3ሺህ 24 የከተማዋ ነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ይቀርፋል ተብሎ ይጠበቃል።

መንግሥት ማኀበራትን በማደራጀት የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት ጥረት እያደረገ መኾኑን ያነሡት ዋና ሥራ አሥኪያጁ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ የወሠዱ ማኀበራት የሚጠበቅባቸውን የሊዝ ክፍያ በመክፈል ወደ ግንባታ መግባት እንዳለባቸውም አሳስበዋል። ከዚህ በፊት በአራት የተለያዩ ዓመታት በማኀበር ተደራጅተው የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ የወሰዱ የከተማዋ ነዋሪዎች በሚፈለገው ደረጃ ወደ ግንባታ በመግባት የመኖሪያ ቤት ችግራቸውን ሲፈቱ አይስተዋልም ብለዋል ዋና ሥራ አሥኪያጁ። ለዚህ ምክንያቱ ማኅበራት የሚጠበቅባቸውን የሊዝ ክፍያ አለመክፈላቸው ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ዋና ሥራ አሥኪያጁ በወቅቱ ወደ ግንባታ ባለመግባታቸው አርሶ አደሩ በድጋሜ መሬቱን መልሶ በመያዙ ከሦስተኛ ወገን አጽዱልን የሚል የመልካም አሥተዳደር ችግር እየፈጠረ መኾኑንም ገልጸዋል። አቶ አንዱዓለም ሙሉ ሰሞኑን የቦታ ርክክብ ላደረጉ ማኀበራት ባስተላለፉት መልእክት ከዚህ በፊት የቤት መሥሪያ ቦታ ከወሰዱ ማኀበራት ችግር በመማር የመኖሪያ ቤት ችግራቸውን ለመፍታት የሊዝ ክፍያን በመክፈል በፍጥነት ወደ ግንባታ መግባት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሊዝ ክፋያ በማይከፍሉ እና ወደ ግንባታ በማይገቡ ማኀበራት ላይ የልማት ክትትል በማድረግ የሊዝ መመሪያውን ተግባራዊ የሚያደረጉ መኾኑንም ዋና ሥራ አሥኪያጁ አንዱዓለም ጨምረው ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኅብረት ባንክ እና ማስተር ካርድ የቅድመ ክፍያ ኅብር ማስተር ካርድ አገልግሎትን አስተዋወቁ።
Next articleየዞኑን ሕዝብ የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስታወቀ፡፡