
አዲስ አበባ: ሚያዝያ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ኅብረት ባንክ እና ማስተር ካርድ በዲጂታል የፋይናንስ አካታችነት ውስጥ ጉልህ ሚና የሚኖረውን የቅድመ ክፍያ ኅብር ማስተር ካርድ አገልግሎት አስተዋውቀዋል። የቅድመ ክፍያ ኅብር ማስተር ካርድ አገልግሎት ደኅንነቱ የተጠበቀ ኢትዮጵያውያን በሌሎች የዓለም ሀገራት የሚኖራቸውን ግብይት ምቹ በኾነ ሁኔታ እንዲያከናውኑ የሚያስችል ነው፡፡
ካርዱ የፋይናንስ አካታችነት እና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማምጣት ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ነው ተብሏል። የኅብረት ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መላኩ ከበደ በይፋዊ የማብሰርያ ፕሮግራም ላይ እንደተናገሩት “በራሳችን ቴክኖሎጂ አቅም የጎለበቱት የኅብር ሞባይል መተግበርያ እና የኮር ባንኪንግ ሲስተም ማሻሻያዎች የውስጥ ፈጠራን ማጎልበት ብቻ ሳይኾን የአገልግሎት ዋስትና እና የተሻለ የደንበኞች ተሞክሮ ዕውን ለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ ናቸው” ብለዋል።
የማስተር ካርድ ምሥራቅ አፍሪካ እና የሕንድ ውቅያኖስ ደሴቶች ሲኒየር ምክትል ፕሬዚዳንት እና ካንትሪ ማናጀር ሻህሪያር አሊ በአጋርነት መሥራት እጅጉን አስፈላጊ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ከኅብረት ባንክ ጋር በኅብር ማስተር ካርድ አገልግሎት የተደረገው ትብብር በኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን በመላው አፍሪካ የፋይናንስ አካታችነት እና ዲጂታላይዜሽን ዕውን ለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነት ማሳያ ነው ብለዋል።
የካርድ አገልግሎቱ ከክፍያ አማራጭነት ባሻገርም ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፉ ገበያ በቀላሉ እና ደኅንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ መሳተፍ የሚያስችላቸው መኾኑን ሻህሪያር አሊ ገልጸዋል። ባለፉት ዓመታት ኅብረት ባንክ ለኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ በቴክኖሎጂ የዘመኑ የፋይናንስ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ ተዓማኒነትን ያተረፈ መኾኑም ተገልጿል።
ዘጋቢ፡- ሳሙኤል ኪሮስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!