
አዲስ አበባ: ሚያዚያ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከ200 በላይ ኢንዱስትሪዎች የሚሳተፉበት የ2016 ዓም የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከግንቦት 1/2016 ዓ.ም እስከ ግንቦት 5/2016 ዓ.ም እንደሚካሄድ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል። የሚካሄደው ኤክስፖ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ማነቆ ለመፍታት አንደሚያግዝ እና ከሀገር ውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት የሚያግዝ መኾኑን መግለጫውን የሰጡት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ ገልጸዋል።
በኤክስፖው ሁሉንም ኢንዱስትሪ ማሳየት ባይቻልም ኢንዱስትሪዎች ያሉበትን ደረጃ ለማሳየት እና ለማስተዋወቅ የገበያ እድልን ለመፍጠር የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡ በኤክስፖው የቆዳ ውጤቶች፣ ጨርቃጨርቅ እና አልባሳት፣ የኬሚካል ኢንዱስትሪዎች፣ አውቶሞቢል ኢንዱስትሪዎች ተሳታፊ እንደሚኾኑ ተጠቅሷል። ከ80 በላይ የሚኾኑት ተሳታፊዎችም መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ናቸው ተብሏል።
በኤክስፖው ከሦስት ቢሊዮን በላይ የሚጠጋ የገበያ ትስስር እንደሚፈጠርም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡ በኤክስፖው የፖሊሲ እና የስትራቴጅ ውይይት የፎቶ ኤግዚብሽን የሽልማት እና የእውቅና ፕሮግራም ለተከታታይ አምስት ቀናት በአዲስ አበባ በሚሊኒየም አዳራሽ ይከናወናል ተብሏል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!