ገጣሚው ካሜራ

26

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ችግር “የፈጠራዎች ሁሉ እናት ናት” ይባላል ነበር። የሰው ልጅ ችግሩን ለማቅላል በሚያደረገው ጥረት የሚፈጥራቸውን የመፍትሄ አማራጮች ለመግለጽ። ዛሬ ላይ ግን የሰው ልጅ ከሚያሳየው የፈጠራ ሥራ መራቀቅ አንፃር በችግር ብቻ ሳይኾን በቅንጦት እና አዳዲስ ነገሮችን በመፍጠር የመደሰት ባሕርይው ምክንያት ለማሰብ የሚከብዱ እና ለአዕምሯችን ቅርበ ያልኾኑ ፈጠራዎችን እያሳየን ነው።

ለዚህ ግርምተ አዕምሮን ለሚፈጥር አዲስ ነገር ደግሞ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሚና ግሩም ነው። ግዑዝ የኾኑ ነገሮች የእኛን የሰው ልጆችን አስተውሎት በመላበስ በአመክንዮ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ፣ ሃሳብን እና ስሜትን ሲገልጹ እንዲሁም ሰዎችን ተክተው ሲሠሩ ወይም ሲያግዙ የምንመለከታቸው አዳዲስ ፈጠራዎች ይህን አስተውሎት የተላበሱ ናቸው።

ኬሊን ካሮሊን እና ሪያን ማተር የተባሉ የፈጠራ ሰዎች ይግረማችሁ ሲሉ ልዩ ቴክኖሎጂን ይዘውልን መጥተዋል። ይህ ቴክኖሎጂ ፎቶግራፍን ካነሳ በኋላ ወደ ግጥም መቀየር የሚያስችል አቅምን የተላበሰ ካሜራ ነው። ይኽን ለመፈጸም ይረዳው ዘንድ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን አካትቷል።

ካሜራው ካለው አገልግሎት በመነሳት የግጥም ካሜራ (poetry camera) የሚል መጠሪያ የተሰጠው ሲኾን በካሜራ ሌንሶች የተፈጠረን ምስል በመረዳት ለምስሉ የሚመጥን ግጥምን ይፈጥራል። ካሜራው እንደ ግብዓት የሚወስደውን ምስል ለመተንተን የሚውሉ ባሕርያትን ለግጥሙ መፍጠሪያነት ይጠቀምበታል።

የፎቶዎችን ይዘት፣ ቀለማትን እና ባሕርያት የመረዳት እና የመመርመር አቅም አለው። ፎቶግራፉን በተረዳው ልክ የሰበሰባቸውን መረጃዎች ተጠቅሞ ስንኞችን ይፈጥራል። እንደ ታይምስ ኦቭ ኢንዲያ ዘገባ የዚህ ፈጠራ መተዋወቅ ለጥበብ ወዳጆች አዲስ አማራጭ ይዞ መምጣቱም ተነግሮለታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በቀጣይ የሚኖረው የአየር ሁኔታ ለበረሀ አንበጣ መራባት እና መሰራጨት ምቹ ሊኾን ይችላል” የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት
Next articleፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መጪውን የትንሣኤ በዓል ምክንያት በማድረግ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች ማዕድ አጋሩ።