
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በቀጣይ ያለው የአየር ሁኔታ ለበረሀ አንበጣ መራባት ምቹ ሁኔታን ስለሚፈጥር ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ መኾኑን የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳወቀ፡፡ ኢንስቲትዩቱ እንዳሳወቀው፣ የሚኖረው ምቹ የአየር ሁኔታ ለበረሀ አንበጣ መራባት እና መሰራጨት ምቹ ሊኾን ስለሚችል የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ክትትል እና ቁጥጥር ሊያደርጉ ይገባል፡፡
በመረጃው መሠረት በወሩ የሚጠበቀው ከፍተኛ መጠን ያለው እርጥበት በአንዳንድ የአፈር ጸባያቸው ውኃ በማያሰርጉ እና ረባዳማ ማሳዎች ላይ የእርጥበት መብዛት እና ውኃ በሰብል ማሳዎች ላይ መተኛት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ይህን ለመከላከልም የውኃ ማንጣፈፍ ሥራዎችን መሥራት እንዲሁም ተዳፋታማ እና ለጎርፍ ተጋላጭ በኾኑ ማሳዎች ላይ ደግሞ ሰብሎች በጎርፍ ተጠርገው እንዳይሄዱ የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮችን በማዘጋዘት የቅድመ ጥንቃቄ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡
በሌላ በኩል የሚጠበቀው እርጥበት ለአርብቶ እና ከፊል አርብቶ አደር አካባዎች የግጦሽ ሳር እና የመጠጥ ውኃ አቅርቦትን ከማረጋገጥ አንጻር የጎላ ሚና ይኖረዋል፡፡ ይህን እድል ለመጠቀምም የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊ የግብርና ግብአቶን በማዘጋጀት ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ መኾኑን ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!