
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የጸረ-ሙስና ኮሚሽኖች ማኅበር የተመዘበሩና ከሀገር የሸሹ ሃብቶችን በቅንጅት ማስመለስ ላይ ያተኮረ ጉባኤ በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው። በመድረኩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ስምንት የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የጸረ ሙስና የሥራ ዘርፍ ኃላፊዎችና ተወካዮች ተገኝተዋል።
በውይይቱ በሙስና የሚሸሹና የሚመዘበሩ ሀብቶችን ለማስመለስ በትብብር መሥራት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑ ተነስቷል። ሙስና በአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እያሳረፈ በመሆኑ ሀገራት በጋራ የሚቆሙበት ወቅት አሁን መሆኑም ተመላክቷል።
የተባበሩት መንግሥታትና የአፍሪካ ኅብረት የጸረ-ሙስና ስምምነቶችን ትግበራ ለማጠናከር በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ተነስቷል።
የፌዴራል የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽነር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ ሀገራት ሙስናን ለመታገል በትብብር መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል። ኢዜአ እንደዘገበው ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ማኅበሩን በምክትል ፕሬዝዳንትነት የመራች ሲሆን በመድረኩ በፀረ ሙስና ትግሉ የጀመረቻቸውን ሥራዎችና ያላትን ልምድ ታካፍላለች።
ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ታንዛንያ፣ ጅቡቲ፣ ኡጋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የጸረ-ሙስና ኮሚሽኖች ማኅበር አባል ሀገራት ናቸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!