ለትንሣኤ በዓል የኀይል መዋዠቅ እና መቆራረጥን ለመቀነስ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እያከናወነ መኾኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

14

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ተቋሙ በትንሣኤ በዓል ዋዜማ እና ዕለት የኀይል መዋዠቅ እና መቆራረጥ ለመቀነስ፣ ከተከሰተም አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቋል። ከዋዜማው ጀምሮ እስከ በዓሉ ዕለት 24 ሰዓት ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ እና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል ጋር ተቀናጅቶ የሚሠራ ግብረ ኃይል በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች ተዋቅሮ ወደ ሥራ መግባቱንም ነው ተቋሙ የገለጸው፡፡

ሊያጋጥም የሚችለውን የኀይል መዋዠቅ እና መቋረጥ ለመቀነስ በውጭ ንግድ ላይ ከተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች በስተቀር ሌሎች ሁሉም የከፍተኛ ኀይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች ከዋዜማው ቀን 7፡00 ጀምሮ እስከ በዓሉ ዕለት ድረስ ከዋናው ግሪድ የሚጠቀሙትን ኤሌክትሪክ እንዲያቋርጡ የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉ ተቋሙ ጠይቋል፡፡

ደንበኞች በቤት ውስጥ የሚገለገሉባቸው የኤሌክትሪክ ቁሳቁሶች ኀይል ቆጣቢ እና ለአደጋ የማያጋልጡ መኾናቸውን እንዲያረጋግጡ አሳስቧል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ጭነት በማይበዛበት ሰዓት በተለይ ከምሽቱ 4፡00 እስከ ንጋቱ 11፡00 ባሉት ጊዜያት መጠቀም የተሻለ አማራጭ መኾኑንም ተቋሙ ጠቁሟል፡፡
የቅድመ ክፍያ አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች ደግሞ በዓሉ ሲደርስ የሚኖረውን አላስፈላጊ ወረፋ ለማስቀረት እንዲችሉ ከወዲሁ የሚበቃቸውን ያህል የኤሌክትሪክ ኀይል አስቀድመው እንዲገዙ /ካርድ እንዲሞሉ/ አሳስቧል፡፡

በአገልግሎት መስጫ ማዕከል ድንገት የኤሌክትሪክ አደጋ ቢያጋጥም በ905 ወይም በ904 ነጻ የስልክ መስመሮች መጠቆም፣ ተቋሙን የሚመለከቱ ሌሎች መረጃዎች መጠየቅ እንዲኹም ጥቆማዎች እና አሥተያይቶች ማቅረብ እንደሚቻል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየስቅለት እና የትንሣዔ በዓላትን ያለምንም የፀጥታ ችግር ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሠራታቸውን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
Next articleየጸረ-ሙስና ኮሚሽኖች ማኅበር አባል ሀገራት ሙስናን ለመታገል በትብብር መሥራት እንደሚገባቸው ተጠቆመ።