
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በመጪዎቹ ቀናት በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የስቅለት እና ትንሣዔ በዓላት ይከበራሉ፡፡ በዓላቱን ያለምንም የጸጥታ ችግር ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሠራታቸውን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ባለፉት ወራት በክልሉ የነበረው የሰላም እጦት እና ግጭት ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ እና ማኅበራዊ ሳንካዎችን ፈጥሯል፡፡ ሕዝቡ ከፀጥታ አካላት ጋር ባደረገው ርብርብ በክልሉ በርካታ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል፡፡ ማኅበራዊ ተቋማት አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፣ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴው በአንጻራዊነት ተመልሷል። ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት ያለምንም የፀጥታ ችግር እየተከበሩ ነው፡፡
በቀጣዮቹ ቀናት የሚከበሩት የስቅለት እና ትንሣዔ በዓላት ሰላማዊ ድባብ እንዲኖራቸው በቂ የፀጥታ ቅድመ ዝግጅት እና ጥንቃቄ ተደርጓል ተብሏል፡፡ በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ዋና ክፍል ኀላፊ ምክትል ኮማንደር መሳፍንት እሸቴ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ እና የክልሉ የፀጥታ መዋቅር የተቀናጁበት እና ከዋዜማው ጀምሮ የሚተገበር ልዩ የፀጥታ እቅድ ተግባራዊ ኾኗል ብለዋል፡፡ እቅዱ የትራፊክ ፍሰቱን እና ስምሪቱን ታሳቢ ያደረገ መኾኑንም ኮማንደር መሳፍንት እሸቴ ነግረውናል፡፡
ከወትሮው የበዓላት ወቅት የፀጥታ ሥራዎች ቅድመ ዝግጅት እና ግንዛቤ ፈጠራ በማኅበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት በኩል ይፈጸም ነበር ያሉት ኮማንደር መሳፍንት አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር መዳረሻ መንገዶቻችን ዘርፈ ብዙ ማድረግ አስፈላጊ ኾኗል ብለዋል፡፡
የክልሉ የፀጥታ መዋቅር መሪዎች በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ላይ ስምሪት ወስደው እየደገፉ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የፀጥታ ሥራ በተወሰኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፎ ብቻ ስኬታማ አይኾንም ያሉት ኮማንደር መሳፍንት የቅድመ ዝግጅት ሥራው በበዓሉ ድባብ ውስጥ ሚና ካላቸው አካላት ጋር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል ብለዋል፡፡ ከሃይማኖት አባቶች፣ መንፈሳዊ አገልጋዮች እና ወጣቶች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን በማካሄድ የስምሪቱ አካል ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
እንደ ኮማንደር መሳፍንት ገለጻ በበዓሉ የቅድመ ዝግጅት ሰሞን ሐሰተኛ የብር ኖቶችን ጨምሮ ሌሎች ሕገ-ወጥ ተግባራት በስፋት ይስተዋላሉ፡፡ የተለያዩ የባንክ አማራጮችን ተጠቅሞ የገንዘብ ዝውውሩን ከስጋት ነጻ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ከትራፊክ እና የትራንስፖርት ስምሪት ጋር ተያይዞ በቂ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ያሉት የሚዲያ ክፍል ኀላፊው ተጠቃሚው ማኅበረሰብ በየቦታው ከቆሙ የትራፊክ እና የትራንስፖርት ባለሙያዎች ጋር በቅርበት መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የእሳት አደጋን ጨምሮ በበዓላት ቀን ሊፈጠሩ ከሚችሉ አደጋዎች እራስን እና ማኅበረሰብን መጠበቅ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ጠጥቶ ማሽከርከር እና መሰል ተገቢ ያልኾኑ ልምዶች ብዙ ጊዜ መራር ዋጋ ሲያስከፍሉ ታዝበናል ያሉት ኮማንደር መሳፍንት ማኅበረሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
ሕዝቡ የተለየ እንቅስቃሴ ሲያስተውል እና ድጋፍ ሲያስፈልገው በቀላሉ በአካባቢው ለሚገኝ የፀጥታ አካል ማሳወቅ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ በተለየ ሁኔታም 0582201327 የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን መረጃ ማዕከል መጠቀም ይችላሉ ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!