
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለተከናወኑት የ’ገበታ ለሀገር’ ፕሮጀክቶች አንድ ሌላ ምዕራፍ መገናወኑ ተገልጿል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተዘጋጀ መርሐ ግብር ፕሮጀክቶቹን ለአማራ፣ ለኦሮሚያ እና ለደቡብ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ማስረከቡም ተገልጿል። በተጨማሪም በገበታ ለሀገር የተገነቡ ሎጆችን ሥራ የማስኬድ ተግባርን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በስካይ ላይት ሆቴል ተቋሙ በኩል እንዲወጣ የስምምነት ፊርማ ሥነሥርዓት ተካሂዷል።
ከአራቱ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ሶስቱ (ሃላላ ኬላ ሎጅ፣ ጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና ሎጅ እና ወንጪ ኢኮ ሎጅ) በቅርቡ መመረቃቸው የሚታወሰ ሲሆን የጎርጎራ ፕሮጀክት ሥራም በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኙም ተገልጿል። በጠቅላይ ሚኒስሩ ከፍተኛ ትኩረት እና አመራር የተከናወነው የ’ገበታ ለሀገር’ ሥራ የብሔራዊው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አንዱ ማዕዘን የሆነውን ቱሪዝምን የማሳደግ አላማ ያለው ነው። እነዚህ ፕሮጀክቶች በመጀመሪያው ፋይናንስ የማሰባሰብ ምዕራፍ የኅብረተሰቡን ድጋፍ በሰፊው ያሰባሰቡ፣ በግንባታቸው ምዕራፍ ግዙፍ የሥራ ዕድል የፈጠሩ ብሎም ታላላቅ የመሰረተ ልማት ሥራዎች እንዲከናወን በር የከፈቱ ናቸው ተብሏል።
በፈጠራ የተሞላ የፕሮጀክት ሥራ እና አሥተዳደር እና ፈጣን አፈፃፀም ምን ሊመስል እንደሚችል ማሳያም እንደኾኑም ነው የተገለጸው። ቀጣይ የሥራ ማስኬድ እና ማሥተዳደር ተግባሩ ለብሔራዊ ሰንደቅ ተሸካሚው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኀላፊነት መሰጠቱም የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ከማስቻሉም ባለፈ ለዓለምአቀፍ የቱሪዝም መዳረሻነት ትውውቅ ከፍ ያለ ዕድል እንደሚፈጥር ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!