
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጸሎተ ሐሙስ በቤት ውስጥ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ጉልባን ማዘጋጀት አንዱ ነው፡ጉልባን ከባቄላ ክክ እና ስንዴ ወይንም የባቄላ ክክ እና የተፈተገ ገብስ ተቀላቅሎ የሚዘጋጅ በዕለቱ ለምግብነት የሚውል ንፍሮ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በባሕር ዳር ሀገረ ሥብከት ደብረ ምህረት ቅድስት ኪዳነ ምህረት ቤተክርቲያን የስብከተ ወንጌል መምህር በትረወንጌል ካሳ እንዳሉት እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ወጥተው ቀይ ባሕርን ሲሻገሩ አቡክተው እና ጋግረው መብላት ስለማይችሉ ያልቦካውን ሊጥ እየጋገሩ ቂጣ መመገብ፤ ንፍሮ ቀቅለው ስንቅ መያዝ የመንገድ ተግባራቸው ነበር፡፡
አባቶችም እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት የወጡበትን ለማስታወስ በየዓመቱ ቂጣ እና ጉልባን ይመገቡ እንደነበር ገልጸዋል። በኢትዮጵያ አብዛኛዎቹ የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው በኢትዮጵያውያን ምእመናን ዘንድ በጸሎተ ሐሙስ ቂጣ እና ጉልባን በቤት ውስጥ ይዘጋጃሉ፡፡
በጸሎተ ሐሙስ የሚዘጋጀው ጉልባን እና ቂጣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ይኸውም ጨው ውኃ እንደሚያስጠማ ኹሉ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በመከራው ወቅት ውኃ መጠማቱን ለማስታወስ እንደኾነም ይነገራል ነው ያሉት መምህር በትረወንጌል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!